ለ17 ዓመታት በባሏ የታሰረችው ብራዚላዊት ነጻ ወጣች

የፎቶው ባለመብት, RIO DE JANEIRO MILITARY POLICE/EPA
ለ17 ዓመታት ከሁለት ልጆቿ ጋር በባሏ ታስራ የነበረችው ብራዚላዊት ነጻ ወጣች።
ግለሰቧ ጉዋራቲባ በተባለ በብራዚል ዋና ከተማ ሪዮ ዴ ጀኔሮ ባለ ሰፈር በሚገኝ ቤት ውስጥ ነበር ባሏ ለዓመታት አስሯት የቆየው።
በሚስቱ ላይ ለዘመናት የዘለቀ ግፍ የፈጸመው ግለሰብ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሏል።
ብራዚላዊቷ ለ17 ዓመታት ስላሳለፈችው እንግልት ከገለጸች በኋላ በአገሪቱ ቁጣ ተቀስቅሷል።
የብራዚል መገናኛ ብዙኃን እንደዘገቡት ባልየው “ከዚህ ቤት የሚወጣው ሬሳሽ ነው” ሲል ሚስቱን ያስፈራራ ነበር።
ጂ1 የተባለው መገናኛ ብዙኃን እንደዘገበው ሉዊዝ አንቶኒዮ ሳንቶስ ሲልቫ የሚባል ግለሰብ ነው ድርጊቱን የፈጸመው።
ጥንዶቹ በትዳር ለ23 ዓመታት ቆይተዋል።
ብራዚላዊቷ እናት ነጻ ከወጣች በኋላ እንደተናገችው፣ እሷና ልጆቿ ለሦስት ቀናት ምግብ ሳይቀምሱ የቆዩባቸው ጊዜያት ነበሩ።
ባሳለፉት ዓመታት ልጆቿ እና ልጆቿ አካላዊ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ጥቃት ይደርስባቸውም ነበር።
ታስረውበት የነበረው ቤት ብርሃን የማያገኝና ቆሻሻ ነበር።
የ19 እና 22 ዓመቶቹ ልጆች የተገኙት ታስረው ሲሆን፣ አካላቸውም ተጎሳቁሏል።
የብራዚሉ ጋዜጣ 'ኦ ዲያ' የአገሪቱን መከላከያ ካፒቴን ዊልያም ኦሊቬራ ጠቅሶ እንደዘገበው፣ ልጆቹ መጀመሪያ ላይ ሲገኙ አካላቸው እጅግ ከመቀጨጩ የተነሳ ወጣቶች ሳይሆን ሕጻናት መስለዋቸው ነበር።
“ስናያቸው በሕይወት አንድ ሳምንትም አይቆዩም ብለን ነበር” ብለዋል።
እናትና ሁለቱ ልጆች ወደ ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፣ በምግብና በውሃ እጥረት ለሕመም መጋለጣቸው ተገልጿል።
እናትና ልጆችን ለ17 ዓመታት ያህል እንዴት ከዚያ ቤት ለማስወጣት እንዳልተቻለ ምርመራ እየተደረገ እንደሚገኝ የብራዚል የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።












