የኤሌክትሪክ ኃይል ለመቆጠብ ሠራተኞች ክራቫት እንዳያስሩ የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስፔን ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ በአሁኑ ሞቃት ወቅት ኃይል ለመቆጠብ በመንግሥትና በግል ተቋማት ያሉ ሠራተኞች ክራቫት ማሰር እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረቡ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት በአውሮፓ የተፈጠረውን የኃይል አቅርቦት እጥረት ለመቋቋም መንግሥታቸው አስቸኳይ የኃይል ቁጠባ እርምጃዎችን ከሰኞ ጀምሮ መውደሰድ እንደሚጀምር ገልጸዋል።
ባለፉት ሳምንታት በአውሮፓ ውስጥ ከባድ ሙቀት ያጋጠመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የሙቀት መጠን ከተመዘገበባቸው የአውሮፓ አገራት መካከል ስፔን አንዷ ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማድሪድ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ክራቫት እንዳላሰሩ ገልጸው፣ ሚኒስትሮቻቸው፣ ሌሎች ባለሥልጣናት እንዲሁም በመንግሥትና በግል ተቋማት ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ክራቫት ማሰር እንዲያቆሙ መክረዋል።
“በዚህም ሁላችንም ኃይል መቆጠብ እንችላለን” ብለዋል ሳንቼዝ።
ይህ ክራቫት ያለማሰር እርምጃ በሥራ ቦታዎች ላይ ሠራተኞች ብዙም ሙቀት እንዳይሰማቸው ስለሚያደርግ የቤት ውስጥ አየር ማቀዝቀዣዎችን በብዛት ስለማይጠቀሙ ኃይል ለመቆጠብ ያስችላል ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
እንዲህ አይነቱን እርምጃ በመውሰድ ስፔን የመጀመሪያዋ አይደለችም፤ ከአስር ዓመት በፊት ጃፓን ሠራተኞች በበጋ ወቅት ለአየሩ ሁኔታ ምቹ አለባበስ እንዲከተሉ የሚያደርግ ዘመቻ አድርጋ ነበር።
በዚህም በሞቃት ጊዜ የቢሮ ሠራተኞች ቀለል ያሉ ልብሶችን እንዲያደርጉ ስታበረታታ ነበር።
በጣም ሞቃት የሆነውን የአየር ሁኔታ ተከትሎ በቅርቡ የዩናይትድ ኪንግደም ፖለቲከኞች በፓርላማ ውስጥ ኮታቸውን ሳያደርጉ መገኘት እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል።
የአውሮፓ አገራት ከሩሲያ የሚያገኙት የኃይል አቅርቦት በመቀነሱ አማራጮችን እየፈለጉ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ መንግሥት ኃይል ለመቆጠብ የሚያስችሉ እርምጃዎችን እያዘጋጀ ሲሆን፣ ተግባር ላይ እንዲሁም ሰኞ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ እርምጃ የአውሮፓ ኅብረት 210 ቢሊዮን ዩሮ በማውጣት የታዳሽ ኃይልን አቅርቦት በማጠናከር የአውሮፓ አገራት ከሩሲያ በሚያገኙት ኃይል ላይ ያላቸውን ጥገኝነት ለመቀነስ ያዘጋጀው ዕቅድ አካል ነው።
ባለፉት ሳምንታት በአውሮፓ እና በሌሎች አገራት ውስጥ የተከሰተውን ከባድ ሙቀት ተከትሎ ኃይል ለመቆጠብ አገራት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። በዚህም ወጪን ለመቀነስና ለአካባቢ ጥበቃ አስተዋጽኦ ለማድረግ አስበዋል።
በዓለም የታየው ከፍተኛ የሙቀት መጠን በኃይል አቅርቦት ላይ ከፈጠረው ጫና ባሻገር በሰው ሕይወት ላይም አደጋን እየደቀነ ነው።
ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ስፔን ውስጥ ከ500 በላይ ሰዎች በካበድ ሙቀት ምክንያት ለህልፈት ተዳርገዋል። የዓለም ጤና ድርጅትም በአውሮፓ የተከሰተው ከባድ ሙቀት “ማስቀረት ይቻል የነበረ” አሳዛኝ ሞቶችን አስከትሏል ብሏል።












