የቀድሞ የትራምፕ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተን በወንጀል ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዶናልድ ትራምፕ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ሆነው ያገለገሉት እና በኋላ ላይ ፕሬዝዳንቱን ክፉኛ በመተቸት የሚታወቁት ጆን ቦልተን የፌደራል የወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የአገሪቱ የፍትህ ቢሮ ሐሙስ ዕለት በቂ መረጃ አለኝ በማለት ሜሪላንድ ውስጥ ክስ አቅርቦባቸዋል። ቦልተንን ጥፋተኛ አይደለሁም ሲሉ መግለጫ አውጥተዋል።
ከሚስጥራዊ መረጃ ጋር በተያያዘ በተደረገው ምርመራ ምክንያት በነሐሴ ወር የኤፍቢአይ ወኪሎች የቦልተንን ቤት እና ቢሮ ፈትሸዋል።
የ76 ዓመቱ ቦልተን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ተቃዋሚ ሆነው ክስ የተመሰረተባቸው ሦስተኛው ግለሰብ ሆነዋል። ጥፋተኛ ከተባሉ ለብዙ አሥር ዓመታት እስራት ሊጠብቃቸው ይችላል።
ሐሙስ ዕለት በግሪንቤልት ሜሪላንድ በሚገኝ ፍርድ ቤት በቀረበ ባለ 26 ገጽ ክስ መሠረት፤ ቦልተን በስምንት የብሔራዊ መከላከያ መረጃዎችን የማስተላለፍ እና በ10 የብሔራዊ መከላከያ መረጃዎችን በሕገ-ወጥ መልኩ በማቆየት ወንጀል ተከሰዋል።
አቃቤ ሕግ የግል ኢሜላቸውን እና ሌሎች የመልዕክት መላላኪያ መተግበሪያዎችን በመጠቀም የአሜሪካን መከላከያ ሚስጥራዊ መረጃን በሕገ-ወጥ መንገድ አስተላልፈዋል በሚል ከሷቸዋል።
"እነዚህ ሰነዶች ስለወደፊቱ ጥቃቶች፣ የውጭ ተቃዋሚዎች እና የውጭ ፖሊሲ ግንኙነቶች መረጃን የያዙ ናቸው" ብሏል።
ቦልተን ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ለእያንዳንዱ ክስ እስከ 10 ዓመት እስራት ሊጠብቃቸው ይችላል። አርብ ለባለስልጣናት እጃቸውን ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲ ክሱን ይፋ ባደረጉበት መግለጫ "ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም" ብለዋል።
ቦልተን ባወጡት በመግለጫ ትራምፕ "እኔን ለመቅጣት ጠይቋል" ሲል ከመክሰስ ባለፈ "ሕጋዊ ኃላፊነቱን" በፍርድ ቤት እንደሚከላከሉ ተናግረዋል።
ቦልተን "[ትራምፕ] ጠላቶቼ ናቸው ብሎ የሚላቸውን ሰዎች ከዚህ በፊት እንዳረገው ሁሉ የፍትህ ቢሮን ተጠቅሞ የመክሰስ ዒላማ ሆኛለሁ" ብለዋል።
የቦልተን ጠበቃ አቤ ሎውል በበኩላቸው ለ45 ዓመታት በሕዝባዊ አገልግሎታቸውን በሚመለከት ደንበኞቸው የያዙትን የማስታወሻ ደብተር ተመርኩዞ ክሱ መመስረቱን ገልጸዋል።
"እንደሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናት አምባሳደር ቦልተን ማስታወሻ ደብተር ይይዝ ነበር። ያ ወንጀል አይደለም" ሲሉ አከልዋል።
ማስታወሻዎቹን "ሚስጥራዊ ያልሆኑ፤ ከቅርብ ቤተሰባቸው ጋር ብቻ የተጋሩ እና እስከ 2021 በኤፍቢኤይ የሚታወቁት ናቸው" ሲሉ ገልጸዋል።
ሲኤንኤን እንደዘገበው ከሆነ ቦልተን መረጃውን ለሚስታቸው እና ለልጃቸው አካፍለዋል ተብሏል።
ያልተፈቀደው መረጃ "ቦልተን የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ በነበሩበት ወቅት የነበሩ ማስታወሻ ደብተሮች" በቤታቸው ውስጥ "ታትመው እና ተከማችተው" ተገኝተዋል።
ቦልተን እአአ በ2019 ከትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን ከኃላፊነታቸው ተባርረዋል።
በ2020 የወጣው 'ዘ ሩም ዌር ኢት ሃፐንድ' የተሰኘ ግለታሪካቸው በትራምፕ ስር የሰሩበትን ጊዜ የሚገልጽ ሲሆን፤ ፕሬዝዳንቱ ስለ ጂኦፖለቲካ ምንም የማያውቁ ተደርገው ተገልጸዋል።
ዋይት ሐውስ መጽሐፉ ምስጢራዊ መረጃዎችን የያዘ እና በትክክል ያልተጣራ ነው በማለት እንዳይታተም ክስ አቅርቧል። ፍርድ ቤት ጥያቄውን ውድቅ በማድረጉ መጽሐፉ ከቀናት በኋላ ለገበያ ቀርቧል።
የዩኤስ የፍትህ ቢሮ ቦልተን ሚስጥራዊ መረጃዎችን በመጽሐፋቸው ውስጥ አላግባብ መጠቀማቸውን በሚመለከት ምርመራ ከፍቷል።
ሐሙስ ዕለት ስለቀረበው ክስ የተጠየቁት ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለ ጉዳዩ እንደማያውቁ ቢናገሩም፤ ቦልተንን "መጥፎ ሰው ነው" ሲሉ አክለዋል።
በጆርጅ ደብሊው ቡሽ አስተዳደር ወቅት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ቦልተን፤ ትራምፕ ላይ ትችት ከሰነዘሩ የቀድሞ ባለስልጣናት መካከል አንዱ ናቸው።
ከመስከረም ወዲህ በወንጀል የተከሰሱ ሦስተኛው የትራምፕ ተቺ ናቸው።
የኒውዮርክ ከተማ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ሌቲሺያ ጀምስ በጥቅምት ወር በባንክ ማጭበርበር ተከሰዋል።
የቀድሞው የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጄምስ ኮሜይ በበኩላቸው ባለፈው መሰከረም መጨረሻ ላይ ኮንግረስን በመዋሸት ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ክሶቹ የተመሰረቱት ትራምፕ የዩኤስ ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን እንዲከሰሱ ካሳሰቡ በኋላ ነው።
"ከእንግዲህ ማዘግየት አንችልም ስማችንን እና ተአማኒነታችንን እየገደለ ነው" ሲሉ በማህበራዊ ሚዲያ ጽፏፈዋል።















