ትራምፕን የመረመሩት የኒውዮርክ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሌቲሺያ ጀምስ በወንጀል ተከሰሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒውዮርክ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሌቲሺያ ጀምስ በፌደራል ወንጀል ተከሰሱ።
በፈረንጆቹ 2023 በትራምፕ ላይ የሲቪል ማጭበርበር ምርመራን የመሩት ጀምስ፤ በምሥራቃዊ ቨርጂኒያ፣ አሌክሳንድሪያ በባንክ ማጭበርበር ወንጀል መከሰሳቸውን የፍርድ ቤት ሰነዶች ያስረዳሉ።
ጀምስን በባንክ ማጭበርበር እና በኖርፎክ ቨርጂኒያ የሚገኝ ቤት ብድርን በተመለከተ ለፋይናንስ ተቋም ሐሰተኛ መረጃ ሰጥተዋል ሲል ዓቃቤ ሕግ ከሷቸዋል።
ጀምስ በመግለጫቸው ላይ ፕሬዚዳንቱ "የፍትህ ስርዓታችንን የማጥቂያ መሳሪያ አድርገውታል" በማለት ከሰዋል።
ትራምፕ በቅርቡ አቃብያነ ሕጎች የወንጀል ክስ እንዲመሰርቱ በይፋ ግፊት አድርገዋል።
"የፌደራል ሕግ አስከባሪዎችን ክስ እንዲመሰርቱ እያስገደደ ነው። ይህ ሁሉ የሆነው የኒውዮርክ ግዛት ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ሆኜ ሥራዬን ስለሠራሁ ነው" ብለዋል።
"እነዚህ ክሶች መሠረተ ቢስ ናቸው። የፕሬዚዳንቱ የአደባባይ መግለጫዎች ግባቸው ምንም ይሁን ምን ፖለቲካዊ ቅጣት ብቻ እንደሆነ በግልፅ ያሳያሉ።"
ጉዳዩን የያዙት የአሜሪካ ዓቃቤ ሕግ ሊንዚ ሃሊጋን በበኩላቸው ጉዳዩ "ማንም ከሕግ በላይ እንዳልሆነ" አረጋግጧል ብለዋል።
"ክሶቹ ሆን ተብሎ፣ የወንጀል ድርጊቶችን እና ከፍተኛ የሕዝብ አመኔታን የሚጥሱ ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
"በዚህ ጉዳይ ላይ ያሉት እውነታዎች እና ሕጎቹ ግልጽ ናቸው። ፍትህ እንዲሰፍን እነሱን መከተላችንን እንቀጥላለን።"
ትራምፕ ጉዳዩን እንዲከታተሉ የቀድሞ የግል ጠበቃቸው ሃሊጋንን የሾሙት የአሜሪካ ዓቃቤ ሕግ ኤሪክ ሲበርት ከሥልጣን መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
ጀምስን ለመክሰስ በቂ ማስረጃ እንዳላገኙ ለፍትህ ዲፓርትመንት በመግለጻቸው ሲበርት ከሥልጣን መነሳታቸው ተዘግቧል።
የጀምስ የመጀመሪያ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ከሁለት ሳምንት በኋላ በኖርፎልክ እንዲሆን ቀጠሮ ተይዞለታል።
የፌደራል መንግሥት ጀምስ በኖርፎልክ ባለ ሦስት መኝታ ቤት እንደገዙ ጠቅሷል።
ንብረቱን እንደ ሁለተኛ መኖሪያቸው በማስያዝ በብድር የገዙ ቢሆንም የጋራ ባለቤትነትን ወይም የቤቱን "የጊዜ መጋራት" አይፈቅድም ሲል ክስ አቅርቦ ነበር።
የክስ መዝገቡ አክሎም ጀምስ ንብረቱን እንደ ሁለተኛ መኖሪያ ቤታቸው "አልያዙትም ወይም አልተጠቀመበትም" ብሏል። ይልቁንም ቤቱ ሦስት አባላት ላሉት ቤተሰብ ተከራይቷል ሲል አክሏል።
"የተሳሳተ መረጃ" በመስጠት ጀምስ ለኢንቨስትመንት ንብረት የማይሰጥ የብድር ውሎችን ለማግኘት ችለዋል ሲል የዓቃቤ ሕግ ክስ ያስረዳል።
ሃሊጋን እንደተናገሩት ከሆነ ጀምስ ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ በአንድ ወንጀል እስከ 30 ዓመት እስራት እና በእያንዳንዱ ክስ እስከ 1 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት ሊቀጡ ይችላሉ።
የጀምስ ጠበቃ አቤል ሎውል በበኩላቸው "ይህ ጉዳይ በፕሬዚዳንት ትራምፕ የበቀል ፍላጎት የተመራ መሆኑ በጣም አሳስቦናል" ብለዋል።
ትራምፕ ባለፈው ወር የፍትህ ቢሮውን የሚመሩትን የዩናይትድ ስቴትስ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ፓም ቦንዲን ጠቅሰው ጀምስን ጨምሮ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን እንዲከሱ በማኅበራዊ ሚዲያ ባስተላለፉት መልዕክት ጠይቀው ነበር።
"ከእንግዲህ ማዘግየት አንችልም ስማችንን እና ታማኝነታችንን እየገደለ ነው" ሲሉ ጽፈዋል።
በጽሑፉ ውስጥ ከተጠቀሱት በርካታ የትራምፕ ባለጋራዎች መካከል ጀምስ አንዷ ነበሩ።
ከጽሑፉ በኋላ በወንጀል የተከሰሱትን የቀድሞ የኤፍቢአይ ዳይሬክተር ጀምስ ኮሜይ እንዲመረምሩ ቦንዲን ጠይቀዋል። ለኮንግረስ የውሸት መረጃ ሰጥተዋል በሚል ቢከሰሱም ረቡዕ ዕለት ጥፋተኛ አይደለሁም ብለዋል።
የፍትህ ቢሮው በትራምፕ የቀድሞ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪ ጆን ቦልተን እና በካሊፎርኒያው ዲሞክራቲክ ሴናተር አደም ሺፍ ላይ ምርመራዎችን መክፈቱንም ተነግሯል።
በጀምስ በቀረበው የማጭበርበር ክስ ትራምፕ የተሻለ የብድር ስምምነቶችን ለማግኘት በሚል መዝገቦችን በማጭበርበር 500 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንዲቀጡ ተደርገዋል። የይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ግን ትራምፕ በማጭበርበር ተጠያቂ መሆናቸውን ቢያረጋግጥም ቅጣቱ ከልክ ያለፈ ነው ሲል ውድቅ አድርጎታል።
በክሱ ወቅት ትራምፕ "ፖለቲካዊ ጥቃት ነው" ሲሉ ጀምስን ከፍርድ ቤቱ ውጭ በተደጋጋሚ ያጠቋቸው ነበር። ጀምስ በበኩላቸው ፍርድ ቤቶች ትራምፕ "ከሕግ በላይ አይደሉም" ብለው ወስነዋል ብለዋል።
ጀምስ ሐሙስ ዕለት እንደተናገሩት ከሆነ ቢሯቸው በትራምፕ እና በድርጅታቸው ላይ የከፈተው ክስ ይደግፋሉ።
የዴሞክራት ፓርቲዋ የኒውዮርክ ገዥ ካቲ ሃችል በበኩላቸው የጀምስ ክስ "ጉልበተኞችን ተጠያቂ የሚያደርጉትን ለመቅጣት የፍትህ ቢሮውን መሳሪያ ከማድረግ የዘለለ አይደለም" ብለዋል።















