የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት በጆ ባይደን ልጅ ላይ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ክስ ለመመስረት ዛቱ

ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ትራምፕ፣ ሀንተር ባይደን ከዶናልድ ትራምፕ ጋር ያገናኛት በወሲብ ንግድ ማሰማራት ጨምሮ በሌሎች ወሲባዊ ወንጀሎች ክስ ተመስርተውበት የነበረው ጄፈሪ ኤፕስቴይን ነው ማለቱን ተከትሎ የአንድ ቢሊዮን ዶላር ክስ ለመመስረታ ዛቱ።

እ.አ.አ በ2025 ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ጋብቻ የመሠረቱት ቀዳማዊት እመቤቷ በጆ ባይደን ልጅ የቀረበባቸውን አስተያየት "ውሸት፣ ንቀት፣ ስም አጥፊ እና የሚያበሳጭ" ሲሉ ሜላኒያን የወከሉት ጠበቆች ገልፀዋል።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ልጅ በወሩ መጀመሪያ በሰጠው ቃለ ምልልስ ወቅት ዶናልድ ትራምፕ ከአወዛጋቢው ጄፈሪ ኤፕስቴይን ጋር ያላቸውን ግንኙነት ሲተቹ ነው ይህን ሀሳብ የሰነዘሩት።

ዶናልድ ትራምፕ የኤፕስቴይን ወዳጅ የነበሩ ሲሆን እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ ከሆነ እ.አ.አ በ2000ዎቹ ወዳጅነታቸው መሻከሩን ተናግረዋል።

ከቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ጠበቆች ለሀንተር ባይደን ጠበቆች የተፃፈ ደብዳቤ አስተያየታቸውን እንዲያስተባብሉ እና ይቅርታ እንዲጠይቁ ካልሆነ ግን የሕግ እርምጃ በመውሰድ ላደረሱት ጉዳት የአንድ ቢሊዮን ዶላር ክስ እንደሚመሰርቱ ይገልፃል።

ቀዳማዊት እመቤቷ መሰቃየቷን ደብዳቤው ሲገልፅ አስተያየቱ በመደጋጋሙ የተነሳ "በገንዘብ እና በዝና ላይ በሚደርስ ጎዳት ተጨንቀዋል" ይላል።

ደብዳቤው አክሎም የባይደን ትንሹ ልጅ በሰዎች ስም የመጠቀም ልምድ አለው በማለት አስተያየቱን የሚደጋግሙት ትኩረት ለማግኘት ነው ሲል ጠቅሷል።

በዚህ ሳምንት ከፊልም ሰሪ አንድሪው ካላኻን ጋር ሰፊ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ሀንተር ባይደን ለሕዝብ ይፋ ያልተደረጉ ሰነዶች ፕሬዝዳንት ትራምፕን በጄፈሪ ኤፕስቴይን ወንጀል ተሳትፎ እንዳላቸው የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

"ኤፕስቴይን ነው ሜላኒያን ለትራምፕ ያስተዋወቀው። ግንኙነታቸው ሰፊ እና ጥልቅ ነው" ብለዋል።

የቀዳማዊት እመቤቷ የሕግ ደብዳቤ ይህ አስተያየት በከፊል የመነጨው ከፕሬዝዳንቱ ግለ ታሪክ ፀሐፊ ጋዜጠኛ ማይክል ወልፍ መሆኑን ይጠቁማል።

ማይክል ወልፍ በቅርቡ ከአንድ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ቀዳማዊት እመቤቷ ባለቤቷን ሲተዋወቁ የጄፈሪ ኤፕስቴይን ወዳጅ እንደነበሩ የሚታወቅ መሆኑን ተናግረዋል።

የቀዳማዊት እመቤት ሜላኒያ ጠበቆች የዘገባውን ይዘት እና አቀራረብ መቃወማቸውን የሚገልፅ ደብዳቤ መፃፋቸውን ተከትሎ መገናኛ ብዙኃኑ ዘገባውን ከገፁ አንስቷል።

ጥንዶቹ እ.አ.አ በ2019 የፍርድ ቤት ጉዳያቸውን እየጠበቁ ባለበት ወቅት በእስር ቤት ራሳቸውን ባጠፉት ጄፈሪ ኤፕስቴይን እንደተዋወቁ የሚያሳይ ማስረጃ የለም።

በቀዳማዊት እመቤቷ የሕግ ደብዳቤ ሀንተር ባይደን ሀሳባቸውን ለመስጠት የተመረኮዙት ከገፁ የተነሳ መሠረተ ቢስ የሆነን ዘገባን መሆኑን ገልጿል።

ቢቢሲ የሀንተር ባይደንን ጠበቆች ለማነጋገር ሞክሯል።

የቀዳማዊት እመቤቷ የሕግ ደብዳቤ ዋይት ሐውስ የጀፍሪ ኤፕስቲንን ፋይል ለሕዝብ ይፋ እንዲያድርግ ጫናዎች በበረቱበት ወቅት የመጣ ነው።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከመመረጣቸው በፊት ፋይሉን ይፋ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፤ ባለፈው ሐምሌ ወር ኤፍቢአይ እና የፍትህ ሚኒስቴር በርካታ ግለሰቦችን የሚወነጅል ስም ዝርዝር የያዘ ፋይል የለም ብለዋል።