በሕጻናት ማቆያ ክፍል ውስጥ በተደበቀ አደገኛ ዕጽ ምክንያት የ1 ዓመት ልጅ ሞተ

የፎቶው ባለመብት, CBS
በአሜሪካዋ ኒው ዮርክ ግዛት በሕጻናት ማቆያ ክፍል ውስጥ ሕጻናት የሚተኙበት ምንጣፍ ስር 'ፌንታሊን' የተሰኘ አደገኛ ዕጽ በመደበቁ የአንድ ዓመት ልጅ ሕይወቱ አለፈ።
ፖሊስ ኒኮላስ ዶሚኒኪ የተባለው የአንድ ዓመት ልጅ በተኛበት በሽታ መልክ ከመጠን በላይ ላይ አደንዛዥ ዕጽ ወስዶ ሕይወቱ አልፏል ብሏል።
ሕይወቱ ካለፈው ሕጻን በተጨማሪ ሌሎች በሕጻናት ማቆያው የነበሩ ሦስት ልጆች ሆስፒታል ገብተዋል።
ፖሊስ ዕድሜያቸው ከስምንት ወር እስከ ሁለት ዓመት የሚሆኑት ልጆች በሕጻናት ማቆያው ፌንታሊን የተባለውን እጅግ አደገኛ አደንዛዥ ዕጽ በአፍንጫቸው ስበዋል ብሎ ያምናል።
ይህን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ በግድያ እና አደንዣ ዕጽ ዝውውር ወንጀል ክሶች በሁለት ግለሰቦች ላይ መስርቷል።
ፖሊስ በሕጻናት ማቆያ ስፍራ ባደረገው ብርበራ ሕጻናት ከሚተኙበት ምንጣፍ ስር የተደበቀ አንድ ኪሎ ግራም የሚመዝን ፌንታሊን አግኝቷል።
የሕጻናት ማቆያ ባለቤት ዲቪኖ ኒኖ እና የሕንጻው አከራይ ካርሊስቶ ብሪቶ የተባሉ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የማንሃተን ዐቃቤ ሕግ ዳሚየን ዊሊያምስ “ተከሳሾቹ የሕጻናት ማቆያን የአደንዛዥ ዕጽ ማከማቻ በማድረጋቸው አራት ልጆችን መርዘው አንዱን ገድለዋል” ብለዋል።
የሕጻናት ማቆያ ሰፍራ ሕጻናት ደኅንነታቸው የሚጠበቅበት ስፍራ እንጂ ለአደንዛዥ ዕጽ የሚጋለጡበት ቦታ መሆን የለበትም ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
ፖሊስ እንደሚለው ከማቆያ ቦታ የተገኘው አንድ ኪሎ ግራም ፌንታሊን 500ሺህ ሰዎችን የመግደል አቅም አለው።
ይህ በክኒን መልክ ለሕመም ማስታገሻነት ተብሎ የሚዘጋጅ መድሃኒት 50 እጥፍ ከሄሮይን በላይ አደገኛ ሲሆን በአሜሪካ ከአደንዛዥ ዕጽ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ እየጨመረ ላለው ሞት ምክንያት ተደርጎ ይቀርባል።
እአአ 2010 ላይ በአሜሪካ ከመጠን በላይ የሆነ አደንዛዥ ወስደው ከሞቱ 40ሺህ ሰዎች ምካከል 10 በመቶ የሚሆኑት ፌንታሊን ተጠቃሚ ናቸው ተብሎ ነበር።
በ2021 ደግሞ በአደንዛዥ ዕጽ ምክንያት 100ሺህ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 66 በመቶ ፌንታሊን ከመጠን በላይ የወሰዱ ናቸው።
በኒው ዮርኩ የሕጻናት ማቆያ ለታዳጊው ሞት እና ለሦስት ልጆች መመረዝ ክስ የቀረበባቸው ሁለቱ ግለሰቦች ጥፋተኛ ሆነው የሚገኙ ከሆነ ቀሪ ዘመናቸውን በእስር ያሳልፋሉ ተብሏል።












