ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
እስራኤል እና ሊባኖስ ‘ታሪካዊ’ የባሕር ድንበር ስምምነት ማድረጋቸውን አሜሪካ አስታወቀች
እስራኤል እና ሊባኖስ ቋሚ የሆነ የባሕር ድንበር ለማቋቋም “ታሪካዊ” የሆነ ስምምነት መድረሳቸውን አሜሪካ አስታወቀች።
ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የሌላቸው ሁለቱ አገራት፤ የባሕር ላይ የድንበር ስምምነት ማድረጋቸው በሜደትራኒያን ባሕር ላይ ያለ የተፈጥሮ ጋዝ አውጥተው እንዲጠቀሙ ይረዳቸዋል ተብሏል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ያኢር ላፒድ አገራቸው ከሊባኖስ ጋር የደረሰችው ስምምነት ደኅንነቷን እንድታስጠብቅ እና ቢሊዮኖችን ወደ ኢኮኖሚዋ እንድታስገባ እንደሚረዳት ገልጸዋል።
የሊባኖስ ፕሬዝዳንት ሚቼል ኡን ደግሞ ስምምነቱን ‘አጥጋቢ’ ሲሉ ገልጸውታል።
ሁለቱ አገራት በሜደትራኒያን ባሕር ላይ 860 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታ አጠቃቀምን በተመለከተ የደረሱት ስምምነት ይዘት ዝርዝር እስካሁን ይፋ አልሆነም።
ይሁን እንጂ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ከዚህ ስምምነት ብዙ ተጠቃሚ የሆነችው እስራኤል ነች።
ካሪሽ የተሰኘው ጋዝ ማውጫ ስፍራ እንዲሁም ቃና የተባለ ጋዝ ሊወጣበት የሚችል አንስተኛ ክፍል ለእስራኤል ተሰጥቷል።
በዚህ ስምምነት መሠረት የቃና አብዛኛው አካል በሊባኖስ ይዞታ ስር የገባ ሲሆን፤ ሌባኖስ ከእስራኤል በኩል ካለ ቦታ ጋዝ የምታወጣ ከሆነ ለእስራኤል ክፍያን ትፈጽማለች።
ዋይት ሃውስ፣ ሁለቱ አገራት ቋሚ የባሕር ድንበር እንዲኖራቸው ከስምምነት በመድረሳቸው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሁለቱን አገራት መሪዎች እንኳን ደስ ያለችሁ ብለዋቸዋል ብሏል።
ባይደን ስምምነቱን በተመለከተ ባወጡት መግለጫ “ስምምነቱ የኃይል አቅርቦት መገኛዎችን በማልማት ሁለቱንም አገራት በመጥቀም የበለጠ የተረጋጋ እና የበለጸገ ቀጠናን ይፈጥራል” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ሁለቱም አካላት የተደረሰውን ስምምነት ለማስከበር ቁርጠኛ አቋም ማሳየት አለባቸው ብለዋል።
ካሪሽ ከሚሰኘው ቦታ ጋዝ በማምረት ለአውሮፓ ኅብረት የመሸጥ የቀደመ ዕቅድ ለነበራት እስራኤል ስምምነቱ ትልቅ ቦታ ይኖረዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚንስትር ላፒድ፤ "ይህ ታሪካዊ ስምምነት የእስራኤልን ደኅንነት የሚያረጋግጥ፣ ወደ እስራኤል ኢኮኖሚ ቢሊዮኖችን የሚያስገባ እና የሰሜን ድንበራችን መረጋጋትን የሚያረጋግጥ ነው" ብለዋል።
የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚንስትር ናጂብ ሚካቲ የስምምነቱ ዝርዝር ለአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቀርቦ ከተመለከቱት በኋላ የስምምነቱ ይዘት ለሕዝብ ይፋ እንደሚሆን ተናግረዋል።
በምጣኔ ኃብት እና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኘው ሊባኖስ፤ ካለችበት የምጣኔ ኃብት ችግር ለመውጣት የጋዝ ክምችት ማግኘት እና መጠቀሟ ትልቅ ትርጉም ይኖረዋል።