በቱርክ ሱፐር ሊግ የፌነርባቼ ተጨዋቾቸ በተሸናፊ ቡድን ደጋፊዎች ጥቃት ደረሰባቸው

ደጋፊ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ትላንት ዕሁድ በቱርክ ሱፐር ሊግ ትራብዞንስፖር እና ፌነርባቼ ባደረጉት ጨዋታ የተሸናፊው ቡድን ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት በፌነርባቼ ተጨዋቾች ላይ ጥቃት አደረሱ።

በፓፓራ ፓርክ የተደረገውን ጨዋታ ፌነርባቼ 3 ለ 2 በሆነ ውጤት ረትቷል። ይህንን ድል ተከትሎ ደስታቸውን እየገለጹ በነበረበት ወቅት ከተቃራኒ ብድን ደጋፊዎች ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።

የፌነርባቼ ተጨዋች የሆኑት ዕውቆቹ ናይጀሪያዊ ኦሴይ ሳሙኤል እና ሚኪ እንዲሁም የቤልጄየም ዜግነት ያለው ባትሽዉዋይ ከተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ራሳቸውን ለመከላከል ሲሞክሩ ታይተዋል።

በሜዳው የተፈጠረው ሁከት እያየለ ሲሄድ የጸጥታ ኃይሎች ወደ ሜዳ ገብተዋል።

የቱርክ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ የርሊካያ ክስተቱን ኮንነውታል። “ከሁሉም በላይ ስፖርት የጨዋ ሰዎች ነው” ያሉት ሚኒስትሩ “በእግር ኳስ ሜዳ ሁከትን መመልከት በምንም ሁኔታ ተቀባይነት የለውም” ሲሉም ተናግረዋል።

በ87ኛው ደቂቃ ባትሽዉዋይ ለክለቡ ጎል ሲያስቆጥር ባለሜዳዎቹ ደጋፊዎች ቁሶችን ወደ ሜዳ ሲወረውሩ በሜዳው ውጥረት ንግሷል።

አንድ ደጋፊ ወደ ፌነርባቼ ተከላከዩ ኦሳይ ሳሙኤል በመሮጥ ጥቃት ያደረሰ ሲሆን ተጨዋቹ በአጸፋው ቡጢ ሲሰነዝር በማህበራዊ ሚዲያ በተሰራጨ ቪዲዮ ታይቷል።

የቱርክ ሊግ የዘንድሮ የውድድር ዘመን ከጀመረ ወዲህ እንዲህ አይነቱ አወዛጋቢ ክስተት ሲያጋጥም ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም።

ደጋፊዎች ጥቃት ሲያደርሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባለፈው በታህሳስ ወር አንድ የክለብ ፕሬዝዳንት በሱፐር ሊግ ጨዋታ ላይ ዳኛ ደብደበው ታግደዋል።

በቱርክ ሱፐር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ ፌነርባቼ ከመሪው ጋላታሳራይ በ2 ነጥብ ዝቅ ብሎ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ሶስተኛ ደረጃ ላይ ያለው የትላንቱ የፌንርባቼ ተጋጣሚ ትራብዞንስፖር ደግሞ በ30 ነጥቦች ዝቅ ብሎ ሶስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

በጨዋታው ባለሜዳው ቡድን ፌነርባቼን ሲመራ የቆየ ቢሆንም ብራዚላዊው ተጨዋች ፍሬድ እና ባትሽዉዋይ ባስቆጠሯቸው ጎሎች አሸናፊ ሆኗል።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የፌነርባቼ ተጨዋቾች ደስታቸውን እየገለጹ ሳለ ነበር የተቃራኒ ቡድን ደጋፊዎች ወደ ሜዳ በመግባት ጥቃት ማድረስ የጀመሩት።