በኬንያ ፖለቲከኞች ለድምጽ ሰጪዎች ጉቦ እየሰጡ የገንዘብ እጥረት አጋጠመ

የኬንያ ገንዘብ ኖቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኬንያ ገንዘብ ኖቶች
ታትሟል

በኬንያ ምርጫ ዕጩዎች የመራጮችን ድምጽ ለማግኘት ጉቦ እየሰጡ በመሆናቸው የ100 እና የ200 ሽልንግ የገንዘብ ኖቶች እጥረት ማጋጠሙ ተገለጸ።

በኬንያ ባንኮች የ100 እና 200 ሽልንግ [የኬንያ ገንዘብ] ኖት እጥረት ያጋጠመው ፖለቲከኞች ለመራጮች ጉቦ እየከፈሉት መሆኑን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፍሬድ ማቲያንጊ ተናግረዋል።

ኬንያ ነሐሴ 03/2014 ዓ.ም. ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለማካሄድ በዝግጅት ላይ የምትገኝ ሲሆን፤ በአገሪቱ በሚካሄዱ ምርጫዎች ዕጩዎች የመራጮችን ድምጽ በገንዘብ የመግዛት ሪፖርት አዲስ አይደለም።

ፍሬድ ማቲያንጊ “ገንዘብ በቦርሳ የያዙ ሰዎች መንገድ ላይ ተሰልፈው ለሚገኙ ዜጎች 200 ሽልንግ ሲሰጧቸው ሳትመለከቱ አይቀርም” ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል፣ ኤኤፍፒ ዘግቧል።

ሚኒስትሩ ቀጣዩ የአገሪቱ ፓርላማ በሕገ-ወጥ መንገድ በተገኘ ገንዘብ የመራጮችን ድምጽ ገዝተው ወንበር በያዙ ፖለቲከኞች ሊሞላ ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

የኬንያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ፤ በሕገ-ወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና ሽብርተኝነትን መደጋፍ በሚመለከት መድረክ ላይ ተገኝተው ንግግር ባደረጉበት ወቅት፤ መሰል የፖለቲከኞች ተግባር አገሪቱ በሙስና ላይ እያካሄደች ያለውን ጦርነት አደጋ ውስጥ የሚጥል ነው ብለዋል።

ፍሬድ ማቲያንጊ በሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ የተሳተፉ ግለሰቦች ሥልጣን ቢጨብጡ እራሳቸውን ለመከላከል ሲሉ የአገሪቱን ሕግ እና መመሪያዎችን ሊቀይሩ ይችላሉም ብለዋል።

በኬንያ ከዚህ ቀደም በነበሩ ምርጫዎች ዕጩዎች ለመመረጥ ከሚያስተዋውቋቸው ርዕዮተ ዓለሞች ይልቅ ዝናቸው እና ለምርጫ ወጪ የሚደርጉት የገንዘብ መጠን በውጤት ላይ ለውጥ ያመጣል።

ከ22 ሚሊዮን በላይ መራጮች ለተመዘገቡበት ምርጫ ማስፈጸሚያ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ አገር 400 ሚሊዮን ዶላር በጀት መድባለች። ይህ ገንዘብ ከሌሎች አገራት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ነው ተብሏል።

ኬንያውያን ከሳምንት በኋላ ለሁለት የሥልጣን ዘመናት አገሪቱን ያስተዳደሩትን ኡሁሩ ኬንያታን የሚተካ አዲስ ፕሬዝዳንት፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላትን እና የግዛት አስተዳዳሪዎችን ይመርጣሉ።

ኬንያን በፕሬዝዳንትነት ለመምራት በምክትል ፕሬዝዳንቱ ዊሊያም ሩቶና በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋ መካከል ጠንካራ ፉክክር ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።