በአሜሪካ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት በተመለሱ በመጀመሪያው ቀን አንድ ተማሪ ስድስት ሰዎችን በጥይት መታ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በዩናይትድ ስቴትስ አዮዋ ግዛት በሚገኝ አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በመጀመሪያው የትምህርት ቀን አንድ ተማሪ ስድስት ሰዎችን በጥይት መትቶ እራሱን አጠፋ።
ፖሊስ እንዳለው በጥይት ከተመቱት ስድስት ሰዎች መካከል አንዱ ሕይወቱ አልፏል።
በፔሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ "በቀላሉ ተዘጋጅቶ" የተቀበረ ፈንጂ መገኘቱንም ፖሊስ ተናግሯል።
ጥቃት ከደረሰባቸው አምስቱ ተማሪዎች ሲሆኑ አንደኛው የትምህርት ቤት አስተዳዳሪ ናቸው።
ህይወቱ ያለፈው ተማሪ የ11 እና 12 ዓመት ታዳጊዎች የሚማሩበት የስድስተኛ ክፍል ተማሪ ነበር።
ጠዋት ላይ የተኩስ ጥቃት መኖሩ እንደተሰማ የመጀመሪያው የፖሊስ መኮንን በደቂቃዎች ውስጥ ወደ ቦታው መድረሱን ፖሊስ ተናግሯል።
የአዮዋ የወንጀል ምርመራ ዲቪዥን ረዳት ዳይሬክተር ሚች ሞርትቨ ከጥቃቱ በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ፖሊሶች ሲደርሱ ተጠርጣሪው ራሱን አቁስሎ አግኝተውታል።
ተጠርጣሪው ዲላን በትለር የተባለ የ17 ዓመት ተማሪ መሆኑ ታውቋል። ፖሊስ እንዳለው ትልቅ መሣሪያ እና ትንሽ የእጅ ሽጉጥ ታጥቆ ነበር።
ሞርትቨ አክለውም ተጠርጣሪው "ጥቃቱ በፈጸመበት ወቅት በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ጽሁፎችን ለጥፏል" ብለዋል።
ከቆሰሉት መካከል አንዱ በአስጊ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን አራቱ ደግሞ ጉዳታቸው ለሕይወታቸው አደጋ አይደለም ብለዋል የፖሊስ መኮንኑ።
የዳላስ ካውንቲ ሸሪፍ አደም ኢንፋንቴ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ጊዜው ጠዋት በመሆኑ “እንደ ዕድል ሆኖ በጣም ጥቂት ተማሪዎች እና መምህራን ነበሩ። ይህም የተጠቂዎችን ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን አስተዋጽኦ አድርጓል ብዬ አስባለሁ” ብለዋል።
የፔሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት የሆነችው ሎሪ ማይኔክ ለአንድ አካባቢው ሬዲዮ ጣቢያ እንደተናገረችው ከስድስት እስከ ሰባት የሚደርሱ የተኩስ ድምጽ ሰምታለች።
በአካባቢው የሚገኝ የቴሌቭዥን ጣቢያ የ15 ዓመት ልጁ በጥይት ተመትቶ የተረፈወን ተማሪ ወላጅ የሆነውን ኬቨን ሼሊን አነጋግሯል።
ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ለመሸሸግ ወደ አንድ ክፍል ከመሮጡ በፊት የሼሊ ልጅ ከኋላው እንደተመታ እንደነገረው ተናግሯል።
የፌደራል የምርመራ ቢሮ (ኤፍቢአይ) እና የአልኮል፣ ትምባሆ፣ የጦር መሳሪያ እና ፈንጂዎች ቢሮ (ኤቲኤፍ) ባልደረቦች በፍጥነት ምላሽ ሰጥተዋል። የአዮዋ የወንጀል ምርመራ ክፍል ምርመራውን እየመራ ይገኛል።
የፔሪ ማህበረሰብ ትምህርት ቤት ዲስትሪክት የቦርድ ፕሬዝዳንት ሊንዳ አንዶርፍ “በጣም አሰቃቂ ነው። ይህ በጣም አስጸያፊ ነው። በጣም አስፈሪ ነው” ማለታቸውን ኤንቢሲ ዘግቧል።
የአዮዋ ገዥ ኪም ሬይኖልድስ በሰጡት መግለጫ “እንዲህ ያለ ነገር ለምን እንደሚከሰት ለመረዳት አይቻልም። ከእያንዳንዱ ተጎጂዎች እና ቤተሰቦቻቸው ጋር አዮዋ ይቆማል” ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ስለ ጥቃቱ ገለጻ ማግኘታቸውን እና ከገዥው ሬይኖልድ ቢሮ ጋር ተገናኝተው እንደነበር ዋይት ሃውስ ዘግቧል።












