የ12 አመቷ ሎላ አሰቃቂ ግድያ የፓሪስ ነዋሪዎችን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ከቷል

ታትሟል

ባሳለፍነው አርብ ከቤተሰቦቿ ጋር በምትኖርበት አፓርታማ ግቢ ውስጥ በፕላስቲክ ማሸጊያ ተጥላ የተገኘቸው የ 12 አመቷ ተማሪ ሎላ አሰቃቂ ግድያ የፓሪስ ነዋሪዎችን ከፍተኛ ድንጋጤ ውስጥ ከቷል።

ቀኑን ሙሉ ትምህርት ቤት የዋለችው ሎላ በተለመደው ሰአቷ ወደ ቤት ሳትመለስ በመቅረቷ ወላጅ አበቷ ስጋት ገብቶት ሲጠባበቅ ቆይቷል።

አመሻሽ ላይ ግን ሎላ በምትኖርበት አፓርታማ ግርጌ ላይ የሎላ አካል በፕላስቲክ ማሸጊያ ሳጥን ውስጥ መገኘቱ ተዘግቧል። የሎላ እጅ እና እግር ታስሮ የተገኘ ሲሆን ፖሊስ ባደረገው የአስከሬን ምርመራ መተንፈስ ባለመቻሏ ሕይወቷ ማለፉን አረጋግጧል። የሎላ አንድ እግር ላይ 0 ሌላኛው ላይ 1 ቁጥሮችን የያዙ ሁለት የፖስታ ማስታወሻዎች ተገኝተዋል።

ፖሊስ ቅዳሜ ማለዳ ላይ በግድያው ዋና ተጠርጣሪ ነች በማለት የ24 ዓመቷን አልጄሪያዊ ተወላጅ ሴት በቁጥጥር ስር አውሏል።

ግለሰቧ ከአፓርታማው ሕንፃ ውስጥ በተወሰደው የደህንነት ቪዲዮ ላይ አርብ ከሰአት በኋላ ከሎላ ጋር አብራ ወደ ዋናው በር ስትገባ ታይቷል።

በመቀጠልም ከህንጻው ወጥታ ዕቃ መያዛ ባልተረጋጋ ሁኔታ ስትሄት መታየቷም ተዘግቧል። አንድ የዓይን እማኝ “ከሕገወጥ የሰዎች የውስጥ አካላት ዝውውር ጋር በተያያዘ” ገንዘብ ለማግኘት በማሰብ እገዛ እንደጠየቀች ተናግሯል።

ሆኖም ፖሊስ እስካሁን ባደረገው ምርመራ አሳማኝ ሆኖ ያገኘው ፅንሰ-ሀሳብ ዳህቢያ ቢ የተሰኘችው ተጠርጣሪ ቋሚ መኖሪያ የሌላት፣ ሥነ ልቦናዋ ያልተረጋጋ እና ድርጊቷ "ለተለየ አላማ ያልተደረገ" እንደሚመስል ገልጿል።

በተጨማሪም ዳህቢያ ቢን እና በመኪናው ውስጥ ያለን የእቃ መያዣን ጭኖ አጓጉዟል ተብሎ የታመነ አንድ የ43 ዓመት ግለሰብም በቁጥጥር ስር ይገኛል። ፖሊስ ዳህቢያ ቢ በግለሰቡ አማካኝነት በፓሪስ ከተማ ዳርቻዎች መዟዟሯን እና ቀጥሎም ሎላ ብሎም የተጠርጣሪዋ እህት ወደምትኖርበት አፓርታማ ይዞ መልሷታል ሲል ገልጿል።

በመቀጠልም ዳህቢያ ቢ እና እህቷ ጮክ ያለ ክርክር ካደረጉ በኋላ የእህቷን ግቢ ለቃ እንደሄደች እና ስትወጣ ግን ይዛው የገባቸውን የእቃ መያዣ ጥላ መሆኑ ተዘግቧል።

ፖሊስ ከ15 አመት በታች የሆነን ሰው በአሰቃቂ ሁኔታ እና አረመኔነት በተሞላበት መልኩ በመግደል ወንጀል ምርመራውን ከፍቶ እያካሄደ ይገኛል። የዳህቢያ ቢም ጉዳይም ምርመራ እየተደረገ እንደሚቆይ ይጠበቃል።

ሰኞ ወደ ትምህርት የጀመሩት የሎላ የተምህርት ቤት ልጆች ብሎም ወላጆች ከፍተኛ ጭንቀት ታይቶባቸዋል። የፈረንሳይ የትምህርት ሚኒስትር እንዲሁም የፓሪስ ከተማ ከንቲባ ትምህርት ቤቱን ጎብኝተዋል። እንዲሁም የስነ ልቦና ድጋፍ ሰጪ ቡድኖች ተማሪዎችን በማጽናናት ላይ መሆናቸውም ታውቀቐል።

የሁለት ልጆች አባት የሆነው ጋስሚ ለ ላ ፓሪስየን ጋዜጣ "ልጄ ቅዳሜና እሁድን ሙሉ ስታለቅስ ነበር፣ ለደቂቃ እንኳን አላሸለበችም" ሲል ተናግሯል። "አሁን በአካባቢያችን ማንንም ማመን አንችልም። ለልጆቼ በጣም እፈራለሁ" ሲልም ተናግሯል። በርካታ ወላጆች እና ልጆች ከፍተኛ ስጋት ውስጥ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የፈረንሳይ ቀዳማይ እመቤት ብሪጊት ማክሮን “ፍፁም አስጸያፊ እና ልንታገሰው የማንችል አሳዛኝ ክስተት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።