"ማንቸስተር ሲቲን ለመቀላቀል ከጫፍ ደርሼ ነበር" ክርስቲያኖ ሮናልዶ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

ክርስቲያኖ ሮናልዶ “የልቡን መሻት” ተከትሎ ማንቸስተር ዩናይትድን በድጋሚ ከመቀላቀሉ በፊት ለማንቸስተር ሲቲ ለመፈረም ከጫፍ ደርሶ እንደነበር ተናግሯል።

ፖርቹጋላዊው የፊት መስመር ተጫዋች በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ክለቡ “ከድቶኛል” ሲል ለቶክ ቲቪ ከተናገረ በኋላ መነጋገሪያ ሆኗል።

የሙሉ ቃለ ምልልሱ የመጀመሪያ ክፍል ረቡዕ ምሽት የተለቀቀ ሲሆን በኦልድ ትራፎርድ ስላለው ጉዳይ በዝርዝር መግለጫ ሰጥቷል።

ሲቲን ሊቀላቀል እንደነበር ሲናገር "እውነት ለመናገር ከጫፍ ደርሶ ነበር" ብሏል።

ሮናልዶ ክለቡን ለቆ ሪያል ማድሪድን ከተቀላቀለ ከ11 ዓመታት በኋላ ነሐሴ 2013 ነበር ከጁቬንቱስ ወደ ኦልድ ትራፎርድ የተመለሰው።

በወቅቱ በሲቲው አለቃ ፔፕ ጋርዲዮላ እንደሚፈለግ ተነግሮ  ነበር።

ሮናልዶ ፍላጎቱን እንደነበር አረጋግጦ ከቀድሞው አሰልጣኙ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ጋር ከተነጋገረ በኋላ ወደ ዩናይትድ ለመመለስ መወሰኑን ተናግሯል።

የ37 ዓመቱ ተጫዋች አክሎም “እንደምታውቀው በማንቸስተር ዩናይትድ ያለኝ ታሪክ፣ ልብህ፣ ከዚህ በፊት የሠራኸውን ስታስታውስ [ውሳኔ ላይ] ለውጥ ያመጣል። በዚያ ላይ ደግሞ ሰር አሌክስ ፈርጉሰን አለ” ብሏል።

"ከሱ ጋር ተነጋገርኩኝ። ‘ወደ ማንቸስተር ሲቲ መምጣት ለአንተ የማይቻል ነገር ነው’ አለኝ። እናም 'እሺ አለቃ' አልኩት” ሲል ገልጿል።

'ወጣት ተጫዋቾች ግድ የላቸውም'

በሆድ ሕመም ምክንያት ዛሬ ፖርቹጋል ከናይጄሪያ ጋር የምታደርገው የወዳጅነት ጨዋታ የሚያመልጠው ሮናልዶ በቃለ መጠይቁ ወቅት የወጣት እግር ኳስ ተጫዋቾችን አመለካከት እና ፕሮፌሽናልነት በመተቸት በዕድሜ የገፉ እና ልምድ ያላቸውን የቡድን አጋሮቻቸውን "አያከብሩም" ሲል ወቅሷል።

“ረሃባቸው [የተለየ ነው]። ነገሮች ቀለል ያሉላቸው ይመስለኛል። ሁሉም ነገር ቀላል ነው። አይለፉም። እናም ግድ የላቸውም” ሲል አክሏል።

"በማንችስተር ዩናይትድ ያሉ ጥቂቶችን ብቻ ማለቴ አይደለም። ነገርግን በሁሉም የዓለም ሊጎች ውስጥ ያሉ ወጣቶቹ ሁሉ እንደ እኔ ትውልድ አይደሉም።

"ነገር ግን እነሱን መውቀስ አይቻልም። ምክንያቱም የሕይወት እና የአዲሱ ትውልድ አካል ነው። አዳዲስ ቴክኖሎጂ ትኩረታቸውን ይከፋፍለዋል" ብሏል።

የ23 ዓመቱ የዩናይትድ እና የፖርቹጋል የቡድን አጋሩን ዲዮጎ ዳሎ ሊያመሰግናቸው ከሚችላቸው ጥቂት ወጣት ተጫዋቾች መካከል አንዱ እንደሆነ ሮናልዶ ገልጿል።

ሮናልዶ አክሎም ሊሳንድሮ ማርቲኔዝ እና ካሴሚሮ በክለቡ የሚያደንቃቸው ሌሎች ተጫዋቾች መሆናቸውንም ተናግሯል።

"በማንቸስተር ዩናይትድ ዳሎትን መጥቀስ እችላለሁ። ወጣት ነው ነገር ግን በጣም ፕሮፌሽናል ነው። በእግር ኳስ ረዥም ዕድሜ እንደሚኖረው አልጠራጠርም።

"ምክንያቱም እሱ ወጣት፣ ብልህ፣ አስተዋይ እና በጣም ፕሮፌሽናል ነው። ምናልባት ማርቲኔዝ እና ካሰሚሮም (ዕድሜው በ30ዎቹ ውስጥ ቢሆንም) ይካተታሉ።  ዳሎን ግን እጠቅሳለሁ" ሲል ተናግሯል።

ሮናልዶ እና ዳሎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'ስለ ራይኒክ በጭራሽ ሰምቼ አላውቅም'

ሮናልዶ ወደ ዩናይትድ ከተመለሰ ከሁለት ወራት በኋላ የቀድሞ የቡድን ጓደኛው ኦሌ ጉናር ሶልሻየር ከአሠልጣኝነት ተሰናበተ።

በምትኩ ራልፍ ራይኒክ እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ ጊዜያዊ አሠልጣኝ ሆነው ተሾሙ።

ጀርመናዊው አርቢ ሌፕሺግ፣ ሻልክ እና ሌሎች በርካታ ክለቦች አሰልጥነዋል። የእግር ኳስ ፍልስፍናቸው እንደ ዩርገን ክሎፕ እና ቶማስ ቱሄል ባሉ አሠልጣኞች ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ይነገርላቸዋል።

ሮናልዶ ግን በሹመቱ እንዳስገረመው ተናግሯል።

"ሰውየው አሠልጣኝ እንኳን አይደለም። እንደ ማንቸስተር ዩናይትድ ያለ ትልቅ ክለብ የስፖርት ዳይሬክተር ሲያመጣ እኔን ብቻ ሳይሆን ዓለምን ሁሉ አስገርሟል" ብሏል።

ስለ ራይኒክ ሰምቶ ያውቅ እንደሆን ሮናልዶ ሲጠየቅ “በጭራሽ ሰምቼ አላውቅም። ካነጋገርኳቸው ሰዎች ማንም አያውቀውም" ብሏል።

"[እሱን] አከብራለሁ። በሙያዬ ውስጥ ያሉ አሠልጣኞችን ሁሉ ‘አለቃ’ ብዬ ልጠራቸው ይገባ ነበር። እሱን ግን እንደ አሠልጣኝ አላየውም። ምክንያቱም እኔ ያልተስማማሁባቸውን አንዳንድ ነጥቦች ስላየሁ ነው” ሲልም አክሏል።

ሮናልዶ እና ሩኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

'የቀድሞ ተጫዋቾች ትችት ምናልባትም የቅናት ይሆናል'

ሮናልዶ የማንቸስተር ዩናይትድ የቀድሞ ተጫዋቾች የሆኑት ዋይኒ ሩኒ እና ጋሪ ኔቪል ባህሪውን በተመለከተ በቅርቡ ጥያቄ ካስነሱ በኋላ ተችቷቸዋል።

ባለፈው ወር ከቶተንሃም ጋር በነበረው ጨዋታ ተቀይሮ ወደ ሜዳ ለመግባት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ሮናልዶ በክለቡ አላስፈላጊ ውዝግብ እየፈጠረ ነው በሚል ሩኒ ተናግሯል።

ፖርቹጋላዊው ስለ ሩኒ ሲናገር “ለምን በጣም በክፉ እንደሚተቸኝ አላውቅም። ይቀናብኝ እንደሆነ አላውቅም” ብሏል።

"እንዲህ ያሉ ሰዎች በእውነት አይገቡኝም። የዜና የፊት ገጽ መሆን ወይም አዲስ ሥራ ወይም ሌላ ነገር ይፈልጉ አላውቅም።

"ምናልባት [ቅናት ሊሆን ይችላል]። ምክንያቱም ጫማውን የሰቀለው በ30 ዎቹ ውስጥ ነው። እኔ አሁንም በከፍተኛ ደረጃ እየተጫወትኩ ነው" ብሏል።

ኔቪልን በተመለከተ ሲናገር ደግሞ “ጓደኞቼ አይደሉም። ባልደረቦቼ ናቸው። ለምሳሌ አብረን እራት አንበላም“ ሲል ተናግሯል።

"ነገር ግን ይህ የጉዞዬ አካል ነው። ሁልጊዜም ይተቹኛል። እኔም ጉዞዬን መቀጠል እና ከሚወዱኝ ሰዎች ጋር መገናኘት አለብኝ” ብሏል።