አሜሪካዊውን የጤና መድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገድሏል የተባለው ባለ ጭምብል ክስ ቀረበበት

ሉዊጂ ማንጃዮኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

አሜሪካዊውን የጤና መድን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብሪያን ቶምፕሰንን ገድሏል የተባለው ሉዊጂ ማንጂዮን የግድያ ክስ እንደተመሰረተበት የኒውዮርክ ግዛት አስተዳዳሪ ገለጹ።

ማንጃዮኒ የአንደኛ ደረጃ ግድያ እና ሁለት የሁለተኛ ደረጃ ግድያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ክሶች ቀርበውበታል። ከእነዚህ መካከል አንዱ "የሽብር" ተግባር የተላበሰ ግድያ የሚል መሆኑን ብራግ ተናግረዋል።

የኒውዮርክ አውራጃ ዓቃቤ ህግ አልቪን ብራግ እንደተናገሩት "ዓላማው ሽብርን ማስፋፋት ነበር" ከማለት ባለፈ ተኩሱን "አስፈሪ፣ በሚገባ የታቀደበት እና ዒላማውን የጠበቀ ግድያ" በማለት አስረድተዋል።

ማንጃዮኒ በተከሰሰበት ክስ ወደ ኒውዮርክ ተላልፎ ይሰጥ እንደሆነ ለመወሰን ታህሳስ 19 ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ቀጠሮ ተይዟል። ተጠርጣሪው ተላልፎ መሰጠቱን ላይቃወም እንደሚችል ብራግ ጠቀሙዋል።

"ተከሳሹ ችሎቱን ሊተው እንደሚችል የሚጠቁሙ ምልክቶች አሉን" ብለዋል ብራግ።

በፔንስልቬንያ ውስጥ ከሽጉጥ ጋር የተያያዙ ክሶች ማንጃዮኒ ላይ በሚቀርብበት በተመሳሳይ ቀን የክስ ሂደቱ መርሐግብር እንደሚጀመር ቀጠሮ ተይዞለታል።

ማክሰኞ ዕለት ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት ብራግ እና የኒውዮርክ ፖሊስ ዲፓርትመንት ኮሚሽነር ጄሲካ ቲሽ ታህሳስ 4 በተፈጸመውንጥቃት ዙሪያ ብዙዎች ማንጃዮኒን ማሞገሳቸውን ተቃውመዋል።

"ቶምፕሰን ከተገደለ በኋላ ባሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ፣ በደም የተጨማለቀውን ግድያ የሚያሞግሱ መኖራቸውን አይተናል። ግድያ አናከብርም እናም የማንንም መገደል ከፍ ከፍ አናደርግም" ሲሉ ጄሲካ ተናግረዋል።

ተጠርጣሪው ከግድያ በተጨማሪ የጦር መሳሪያ በመያዝ እና በሃሰተኛ ማስረጃ ክስ ቀርቦበታል። በቀረበቡት የአንደኛ ደረጃ ግድያ እና ሁለተኛ ደረጃ የሽብር ግድያ ተግባር ከተፈረደበት ማንጃዮኒ ያለይቅርታ ዕድሜ ልክ እስራት ሊተላለፍበት ይችላል።

ስለ ልዩ የሽብርተኝነት ክሱ የተጠየቁት ብራግ "ይህ ሽብር ለመቀስቀስ ታስቦ የተደረገ ግድያ ነው" ሲሉ መልሰዋል።

የዩናይትድ ሄልዝኬር ዋና ስራ አስፈፃሚ ቶምፕሰን በጥይት ተመትተው ከተገደሉ ከአምስት ቀናት በኋላ ማንጃዮኒ በአልቶና ፔንሲልቬንያ በሚገኘው ማክዶናልድ ውስጥ በሐሰተኛ መታወቂያ እና "ሽጉጥ" ይዞ በቁጥጥር ስር መዋሉን ፖሊስ ተናግሯል።

ጠበቃው ቶማስ ዲኪ በበኩላቸው የማንጃዮኒን ሽጉጥ ከወንጀሉ ጋር የሚያገናኘውን ማስረጃ አላየሁም ብለዋል።

የኒውዮርክ ዓቃብያነ ህግ ባለፈው ሳምንት በማንጃዮኒ ላይ የክስ ማስረጃቸውን ለዳኞች ማካፈል ጀምረዋል።

የ26 ዓመቱ ማንጃዮኒ ተላልፎ ከተሰጠ በሪከር ደሴት ወይም በሌላ የኒውዮርክ እስር ቤት ሊታሰር ይችላል።

የዩናይትድ ሄልዝኬር ዋና ስራ አስፈፃሚ ቶምፕሰን

የፎቶው ባለመብት, Shutterstock

በማንጃዮኒ ላይ የቀረበው ማስረጃ በወንጀል ቦታ ከተገኙት ጋር የጣት አሻራ ጋር ተመሳሳይ መሆናቸውን ያካትታል ሲሉ ኮሚሽነር ጄሲካ ተናግረዋል።

ብራግ በበኩላቸው ተጠርጣሪው ኒውዮርክ ደርሶ በማንሃተን ሆስቴል ውስጥ የውሸት መታወቂያ በመጠቀም ለ10 ቀናት ከቆየ በኋላ ቶምፕሰን ላይ ጥቃቱን ፈጽሟል።

ማንጃዮኒ በቁጥጥር ስር ሲውል ሽጉጥ፣ ሃሰተኛ መታወቂያ፣ ፓስፖርት እና "ተነሳሽነት እና አስተሳሰብን" የሚያመለክት በእጅ የተጻፈ ሰነድ መገኘቱን ፖሊስ ተናግሯል።

በኒውዮርክን የተከፈቱ ክሶችን በተመለከተ በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኒውዮርክ ፖሊስ የመርማሪዎች ዋና አዛዥ ጆሴፍ ኬኒ በህዳር ወር ሳን ፍራንሲስኮ ውስጥ ለልጇ መጥፋቱን ሪፖርት ካደረገችው ከተጠርጣሪው እናት ጋር ግንኙነት መፈጠሩን ጠቁመዋል።

እንደ ኬኒ ገለጻ እናቱ ልጇን ተጠርጣሪው ስለመሆኑ ባታውቅም ግን "እሱ ሊያደርገው የሚችለው ነገር ሊሆን ይችላል" ስትል ተናግራለች።

ማንጃዮኒ በሃሰተኛ ማስረጃ፣ መሳሪያን ያለፍቃድ በመያዝ፣ መዝገቦችን ወይም መታወቂያዎችን በማበላሸት፣ የወንጀል መሳሪያዎችን በመያዝ እና ለፖሊስ የሃሰት መታወቂያ በመስጠት ወንጀል በፔንስልቬንያ ውስጥ ክስ ተመስርቶበታል።

ማንጃዮኒ የኒው ዮርክ ፍርድ ቤት ውሳኔን በሃንቲንግዶን ግዛት፣ ፔንስልቬንያ ውስጥ ባለው የሃንቲንግዶን ስቴት ማረሚያ ተቋም ሆኖ ይጠብቃል።

ተከሳሹ ያቀረበው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ተደርጓል።