ራሽፎርድ፣ ትሬንት. . . በጥር የዝውውር መስኮት እነማን ሊሄዱ ይችላሉ?

ኩኛ፣ ራሽፈርድ፣ ትሬንት እና ዙባሜንደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የጥር የተጫዋቾች ዝውውር ውስብስብ እና አስቸጋሪ መሆኑ ይነገርለታል።

የጨዋታዎች መደራረብ፣ ጉዳት እና በሊጉ ለመቆየት የሚደረጉ ፉክክሮችን ከግምት በማስገባት በርካታ ፕሪሚየር ሊጉ ቡድኖች ተጨዋቾችን እንደሚያስፈርሙ ይፋ አድርገዋል።

የጥር የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ለአንድ ወር ይዘልቃል።

ቢቢሲ ስፖርት በቀጣይ አንድ ወር ክለብ ሊቀይሩ የሚችሉ ናቸው ያላቸው ስመጥር ተጫዋቾችን እንደሚከተለው ቃኝቷል።

ማርከስ ረሽፎርድ (ማንቸስተር ዩናይትድ)

ማርከስ ረሽፎርድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሁን ማርከስ ረሽፎርድ ከክለቡ ጋር ይለያያል ወይ ከሚለው ይልቅ መቼ ይለያያል የሚለው ነው ምላሽ ያላገኘ የሚመስለው። ከጥቂት ሳምንታት በፊት አጥቂው "ለአዲስ ፈተና ተዘጋጅቻለሁ" ማለቱ ይታወሳል።

ከዩናይትድ አካዳሚ የተገኘው ረሽፎርድ 426 ጨዋታዎችን አከናውኖ 138 ጎሎችን አስቆጥሯል። በ2022/23 የውድድር ዓመት 30 ጎሎችን በማስቆጠር ድንቅ ዓመት አሳልፏል።

ያለፉትን 18 ወራት ባሳየው ደካማ እንቅስቃሴ ግን ተችቶችን እያስተናገደ ነው። ከዩናይትድ ጋር ያለው እና ከፍተኛ ክፍያ የሚያስገኝለት ውል ለዝውውሩ እንቅፋት ሊሆን ይችላል።

የኮንትራት ማብቂያ ጊዜ፡ ሰኔ 2028

መዳረሻ የሚሆኑ ክለቦች፡ ፒኤስጂ፣ ባርሴሎና እና እንደ አል-አህሊ፣ አል-ኢትሃድ እና አል-ቃዲሳህ ያሉ የሳዑዲ ፕሮ ሊግ ክለቦች

ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ (ሊቨርፑል)

ትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሊቨርፑል ሦስት ኮከብ ተጫዋቾቹ የገቡት ውል ከስድስት ወራት በኋላ ይጠናቀቃል። ቨርጂል ቫንዳይክ እና ሞሐመድ ሳላህ ሊቆዩ እንደሚችሉ ፍንጭ የሰጡ ሲሆን የትሬንት አሌክሳንደር-አርኖልድ ጉዳይ ግን አለየለትም።

ከወራት በፊት የኮንትራት ማራዘም ጉዳይ በይፋ እንደማይነገር ማሳወቁ ደግሞ ተጫዋቹ በሊቨርፑል ያለው ቆይታ ላይ ጥያቄ አስነስቷል።

ሊቨርፑል ፕሪሚየር ሊጉን በመምራት ላይ ሲሆን በሻምፒዮንስ ሊግ እና በካራባኦ ዋንጫም ተስፋ መሰነቁ የተጫዋቹን ዝውውር እንዲያስቆም ምክንያት ቢሆነውም ምን ያህል በዚህ መልኩ ይዘልቃል የሚለው ጥያቄ ይጭራል።

የኮንትራት ማብቂያ ጊዜ፡ ሰኔ 2025

መዳረሻ የሚሆኑ ክለቦች፡ ሪያል ማድሪድ፣ ማንቸስተር ሲቲ

ማርቲን ዙቢሜንዲ (ሪያል ሶሲዬዳድ)

ማርቲን ዙቢሜንዲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሊቨርፑል ባለፈው ክረምት ማርቲን ዙቢሜንዲን ለማስፈረም ከጫፍ ደርሶ ነበር። ሮድሪን በጉዳት ያጣው ማንቸስተር ሲቲም በቦታው ላይ ተጫዋች ይፈልጋል።

ስፔን በ2024 የአውሮፓ ዋንጫን ስታነሳ ዙቢሜንዲ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል። ውሉን ለማፍረስም 51.7 ሚሊዮን ፓውንድ ያስፈልጋል።

ስለዝውውሩ የሚናፈሰውን ጉዳይ "በጥሩ መንገድ ይዤዋለሁ" ሲል ዙቢሜንዲን የዝውውር መስኮቱ ከመከፈቱ በፊት ተናግሯል።

ሶሲዬዳድ በላሊጋው የደረጃ ሰንጠረዥ አጋማሽ ላይ መገኘቱ ተጫዋቹ ሌሎች ክለቦችን እንዲመለከት ምክንያት ሊሆነው ይችላል።

የኮንትራት ማብቂያ ጊዜ፡ ሰኔ 2027

መዳረሻ የሚሆኑ ክለቦች፡ ሊቨርፑል፣ አርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ባርሴሎና

ቤን ቺልዌል (ቼልሲ)

ቤን ቺልዌል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የ28 ዓመቱ ቤን ቺልዌል በብቃቱ ማማ ላይ ሆኖ ክለቡን ማገልገል ሲገባው ከቼልሲ ቡድን ውጭ ተደረጓል።

ከሌስተር በ2020 ክለቡን የተቀላቀለው ተጫዋቹ ዘንድሮ በካራባኦ ዋንጫ ከባሮው ጋር በተደረገ ጨዋታ ለ45 ደቂቃ ብቻ ተሰልፏል። ባለፈው የዝውውር መስኮት ከክለቡ ለመልቀቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ክለቡን "ለመልቀቅ ከሚያስቡ" ተጫዋቾች መካከል አንዱ ቺልዌል መሆኑን ጠቅሰው ቼልሲ "መፍትሔውን እንደሚፈልግ" አስታውቀዋል።

በደሞዙ ምክንያት በውሰት ሊዘዋወር እንደሚችል ተገምቷል።

የኮንትራት ማብቂያ ጊዜ፡ ሰኔ 2027

መዳረሻ የሚሆኑ ክለቦች፡ ጁቬንቱስ፣ ብሬንትፎርድ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ፣ ዌስት ሃም፣ ፌነርባቼ

ማቲየስ ኩኛ (ዎልቭስ)

ማቲየስ ኩኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ማቲየስ ኩኛ ቡድኑ ደካማ ሆኖ በተያበት በዘንድሮው የውድድር ዓመት ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።

ተጫዋቹ ባለፉት 11 ጨዋታዎች ሰባት ጎሎችን አስቆጥሮ አራት ለኳስ የሚሆኑ ኳሶችን አቀብሏል።

ብራዚላዊው አጥቂ ከአትሌቲኮ ማድሪድ ነበር በ35 ሚሊዮን ፓውንድ ዎልቭስ የደረሰው።

ቡድኑ ተጫዋቹን ማቆየት ወይንም ጥሩ አቋም ላይ ባለበት በአሁኑ ወቅት በጥሩ ገንዘብ ማዘዋወር በሚሉ አማራጮች መካከል ወድቋል።

የኮንትራት ማብቂያ ጊዜ፡ ሰኔ 2027

መዳረሻ የሚሆኑ ክለቦች፡ ሊቨርፑል፣ አርሰናል፣ ማንቸስተር ሲቲ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ኒውካስል

ሌሎች ሊሳኩ የሚችሉ ዝውውሮችስ?

የቼልሲ አሰልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ካርኒ ቹኩሜካ ለሽያጭ መዘጋጀቱን እና ሴዛር ካሳዲ ደግሞ በውሰት እንደሚዘዋወር ተናግረዋል።

ዳኒ ኦልሞን ማስመዝገብ ያልቻለው ባርሴሎና ተጫዋቹን የማቆየት ዕድሉ ጥያቄ ውስጥ ወድቋል።

የኒውካስሉ አጥቂ አሌክሳንደር ኢዛክ ወደ አርሰናል ይዘዋወራል በሚል ስሙ ተደጋግሞ ተነስቷል።

የባየር ሊቨርኩሰኑ ፍሎሪያን ሪዝ እና የኒውካስሉ ብሩኖ ጉማሬሽ ወደ ማንቸስተር ሲቲ ሊዘዋወሩ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው።

አዲሱ የማንቸስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም ቡድናቸውን ለማደረጃት ሁለት ተጫዋቾችን ሊያስፈርሙ ይችላሉ።

በስፖርቲንግ ከአሞሪም ጋር የሠራው አጥቂው ቪክቶር ጋዮከሪስ ስሙ ከአርሰናል እና ከዩናይትድ ጋር ተያይዟል።

ጆሹዋ ዚርክዚ እና አንቶኒ ደግሞ ከዩናይትድ ሊለቁ የሚችሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ከሊል ጋር ያለው ውል በሰኔ ወር የሚጠናቀቀው አጥቂው ጆናታን ዴቪድ ከበርካታ የፕሪሚየር ሉጉ ክለቦች ጋር ስሙ ተያይዟል።

የፒኤስጂው አጥቂ ራንዳል ኮሎ ሙዋኒ ያቀናባቸው ተብለው የተጠቀሱትን ክለቦች ስም ለመዘርዘር ቦታም አይበቃም።

ሚኪ ቫብ ደ ቬን እና ክርስቲያን ሮሜሮን በጉዳት ያጣው ቶተንሃም ለተከላካይ ግዢ ሊሰማራ ይችላል።

ጎል የማግባት ችግር ያለበት ክሪስታል ፓላስ አጥቂ ለማስፈረም ሊንቀሳቀስ እንደሚችል ይገመታል።