ባይደን የሩሲያን ጦርነት ለማስቆም ከፑቲን ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን።

የፎቶው ባለመብት, SHAWN THEW/EPA

የምስሉ መግለጫ, የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የአሜሪካው አቻቸው ጆ ባይደን።
ታትሟል

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሩሲያ እና የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም ከሩሲያው አቻቸው ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ገለጹ።

ባይደን “ጦርነቱን ለማቆም አማራጭ የመፈለግ ፍላጎት በውስጡ ካለ” ከቭላድሚር ፑቲን ጋር ለመገናኘት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ባይደን ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር ሆነው በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ፑቲን ጦርነቱን የማቆም ፍላጎት አለማሳየታቸውን አጽንጾት ሰጥተው ተናግረዋል።

ሁለቱ መሪዎች በመግለጫቸው የሩሲያን ጦርነት በመቃወም እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። የአሜሪካ እና የፈረንሳይ መሪዎች ይህን ያሉት ዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት ከ10 ሺህ እስከ 13 ሺህ ወታደሮቿ እንደተገደሉ ከገለጸች በኋላ ነው።

ከዚህ ቀደም ሩሲያም ትሁን ዩክሬን በጦርነቱ ምክንያት በሰው ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ አሃዝ አይሰጡም።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት አማካሪም በጦርነቱ የኪዬቭ ሠራዊት ላይ የደረሰውን የሞት ጉዳት በተመለከተ የሰጡት ቁጥር በአገሪቱ ጦር አልተረጋገጠም።

ከአንድ ወር በፊት የአሜሪካ ከፍተኛ የጦር ጄኔራል የሆኑት ማርክ ሚሊ ከጦርነቱ ጅማሮ አንስቶ 100ሺህ የዩክሬን እንዲሁም 100 ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ተገድለዋል ወይም ቆስለዋል ብለው ነበር።

የዜሌንስኪ አማካሪ ማይክሃሎ ፖዶላይክ ለዩክሬን ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲናገሩ ዩክሬን በጦር ሜዳ ስለሚገደሉ የሠራዊት አባላት በግልጽ ስትገልጽ ቆይታለች ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጦርነቱ ምክንያት የሞቱ ሰላማዊ ሰዎች ቁጥር “ከፍተኛ” መሆኑን የጠቀሱት የፕሬዝዳንቱ አማካሪ፤ ከጦርነቱ መቀስቀስ ጀምሮ በሩሲያ በኩል የተገደሉ ወታደሮች ቁጥር እስከ 100 ሺህ እንደሚጠጋ ገልጸዋል።

አማካሪው ይህን ይበሉ እንጂ ከትናንት በስቲያ ረቡዕ ኅዳር 21/2015 ዓ.ም. የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ኃላፊ ኡርሱላ ቮን ደር ለየን 100 ሺህ የዩክሬን ወታደሮች ተገድዋል ብለው ነበር።

የኮሚሽኑ ኃላፊ ይህን ካሉ በኋላ የኅብረቱ ቃል አቀባይ አሃዙ ስህተት መሆኑን በመግለጽ 100ሺህ የተገደሉት ብቻ ሳይሆን የቆሰሉ ወታደሮችንም ይጨምራል ብለዋል።

የኮሚሽኑ ኃላፊ በሠራዊት አባላት ላይ ደርሷል ካሉት ጉዳት በተጨማሪ ወደ 20ሺህ የሚጠጉ ዩክሬናውያን ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሰዋል።

ፕሬዝዳንት ባይደን እና ማክሮን በዋይት ሐውስ ከተወያዩ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ የዩክሬንን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለማረጋገጥ ዘላቂ የሆነ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

መሪዎች በመግለጫቸው ለዩክሬን የአየር መከላከያ ሥርዓት አቅርቦትን ማፋጠን እና በሁለት ሳምንታት ውስጥ በዩክሬን ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ኮንፍረንስ ፓሪስ ላይ ለማዘጋጀት መታቀዱን አመልክተዋል።

የሁለቱ መሪዎች የጋራ መግለጫ ከመውጣቱ በፊት የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አውሮፓውያን አገራት ድርድር ለማድረግ ያቀረቡት ተጨባጭ ነገር የለም ሲሉ ቅሬታ አሰምተው ነበር።

ማክሮን ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከሩሲያ ፕሬዝዳንት ጋር ለመነጋገር አቅጃለሁ ይበሉ እንጂ፣ በጉዳዩ ላይ ለሩሲያ የቀረበ ጥያቄ አለመኖሩን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረው ገልጸዋል።

ላቭሮቭ የቀድሞ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ጆን ኬሪ ችግሮችን ለመፍታት እና እውነተኛ ንግግር ለማድረግ የሚችሉ ናቸው ሲሉ ስማቸውን ጠቀሰዋል።