አሜሪካ እና አጋሮቿ በሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣሉ

የሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል ሙከራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አሜሪካ እና የሩቅ ምሥራቅ አጋሮቿ በሰሜን ኮሪያ የሚሳኤል ግንባታ ላይ ጉልህ ሚና አላቸ ባሏቸው ሦስት ግለሰቦች ላይ ማዕቀብ ጣሉ።

ማዕቀቡ የተጣለባቸው ሦስቱ የሰሜን ኮሪያ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጆን ኢል ሆ፣ ዩ ጂን እና ኩም ሱ ጂል ይባላሉ።

በግለሰቦቹ ላይ ማዕቀብ መጣሉን ይፋ ያደረገው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት፣ እነዚህ ባለሥልጣናት በሰሜን ኮሪያ ሚሳኤል ግንባታ ላይ “ጉልህ ሚና ተጫውተዋል” ብሏል።

ሰሜን ኮሪያ በተያዘው የፈረንጆች ዓመት ከ60 በላይ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን እና አህጉር አቋራጭ የሆኑ በርካታ ባሊስቲክ ሚሳኤሎችን ለሙከራ ተኩሳለች። 

ከአሜሪካ ጋር በመሆን በግለሰቦቹ ላይ ማዕቀብ የጣሉት ጃፓን፣ ደቡብ ኮሪያ እና የአውሮፓ ኅብረት አገራት ናቸው።

ሰሜን ኮሪያ በምዕራባውያን እና የምዕራባውያን አጋር በሆኑ የእስያ አገራት ለዓመታት የዘለቁ ሌሎች ማዕቀቦች ተጥሎባት ይገኛል።

ዛሬ ይፋ የሆነው አዲስ ማዕቀብ የተጣለባቸው ግለሰቦች በአሜሪካ የሚገኝ ንብረታቸውን እንዳያንቀሳቅሱ የሚያግድ ሲሆን፣ ከንግድ ተቋማት እና ከግለሰቦች ጋር የንግድ ልውውጥ ማድረግ አይችሉም።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ማዕቀቡ በግለሰቦቹ ላይ የተጣለው ከደቡብ ኮሪያ፣ ጃፓን እና ከአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ጋር በቅርብ በመጣመር መሆኑን አስታውቋል።

ፒዮንግያንግ ከእአአ 2006 እስከ 2017 6 የኒውክለር ጦር መሳሪያ ሙከራ ያደረገች ሲሆን፣ 7ኛ ሙከራዋን ለማድረግ ዝግጅት ማጠናቀቋ ተመልክቷል።

የሰሜን ኮሪያ ጉዳዮች አጥኚዎች እንደሚሉት ሰሜን ኮሪያ የመካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎቿን ለማሻሻል እና የጦር አቅሟን ለማጠናከር እየሰራች ትገኛለች።

ሰሜን ኮሪያ በወጣቱ መሪ ኪን ጆንግ-ኡን መመራት ከጀመረች ወዲህ በኒውክሌር ግንባታ እና ሚሳኤል ሙከራ የበለጠ ተጠምዳለች።

ፒዮንግያንግ በኪም ጆንግ-ኡን አስተዳደር ስር አራት የኒውክሌር ሙከራዎችን አድርጋለች።

የአሜሪካ ግምጃ ቤት በበኩሉ ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ ያካሄደቻቸው ሙከራዎች የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ተፈጻሚ መሆን እንዳለበት የሚያረጋግጥ ነው ብሏል።

ግምጃ ቤቱ የፀጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ ሰሜን ኮሪያ ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ለማበልጸግ የሚያስፈልጋትን ቴክኖሎጂ፣ ግብዓቶችን እና ገንዘብ እንዳታገኝ ያደርጋታል ይላል።

ግምጃ ቤቱ ይህን ይበል እንጂ አንዳንድ አሜሪካውያን ተንታኞች ሰሜን ኮሪያ የተጣሉባት ማዕቀቦች ጅምላ ጨራሽ መሳሪዎችን ከማበልጸግ ስላላገዳት ይህም ማዕቀብ የረባ ለውጥ አያመጣም ይላሉ።