አራት ተማሪዎችን ተኩሶ የገደለው አሜሪካዊ ታዳጊ አባት በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ

ጄምስ ክሩምብሌይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

አራት ተማሪዎችን በሚቺጋን ትምህርት ቤት ተኩሶ የገደለው አሜሪካዊ ታዳጊ አባት በግድያ ወንጀል ጥፋተኛ ተባለ።

አባትየው ጄምስ ክሩምብሌይ ለ15 ዓመት ታዳጊ ልጁ ተኩሶ የገደለበትን ሽጉጥ በመግዛት እንዲሁም የአዕምሮ ጤናውንም ችላ በማለት ነው የተከሰሰው።

ታዳጊው በአውሮፓውያኑ 2021 ጥቃቱን አድርሶ ተማሪዎቹን የገደለው።

ዳኞች ብያኔ ላይ ከመድረሳቸው በፊት ለአንድ ቀን ያህል ተወያይተዋል።

የታዳጊው እናት ጄኔፈር ክሩምብሌይ በተመሳሳይ ክስ ጥፋተኛ ሆና የተገኘች ሲሆን በሚቀጥለው ወርም ቅጣቱ ይበየንባታል ተብሏል።

ፍርድ ቤት ሐሙስ ዕለት በዋለው ችሎቱ ብያኔውን ሲያሰማ ግለሰቡ ብዙም ስሜት እንዳልተነበበትም ተገልጿል።

ባልና ሚስቱ በልጃቸው ግድያ ወንጀል ተከሰው ጥፋተኛ ሲባሉ በአሜሪካ ታሪክ የመጀመሪያው ነው።

ልጃቸው ኤታን በሽጉጥ የገደላቸው የ16 ዓመቷ ታቴ ማየር፣ የ14 ዓመቷ ሃና ሴት ጁሊያና፣ የ17 ዓመቷ ማዲሲን ባልድዊን እና የ17 ዓመቱ ጀስቲን ሽሊንግ ናቸው።

ህይወታቸው ከተቀጠፉትም በተጨማሪ ሰባት ሰዎችም ቆስለዋል።

በአሁኑ ወቅት 17 ዓመቱ የሆነው ልጃቸው ከሶስት ዓመታት በፊት ኦክስፎርድ በተሰኘው ትምህርት ቤት አራት የክፍል ጓደኞቹን በመግደልም ጥፋተኛ ተብሎ የእድሜ ልክ እስራት ላይ ይገኛል።

ከውሳኔውም በኋላ ሃና የተባለችው ሟች አባት ስቲቭ ሴይንት ጁሊያን እንደተናገሩት ባልና ሚስቱ ተክስሰው ጥፋተኛ መባላቸው በአሜሪካ ውስጥ ከመሳሪያ ጥቃት ጋር በተያያዘ “የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች” እንደሆኑ ተናግረዋል።

“ልጆቻችን በጅምላ ግድያ በየቀኑ እየረገፉ ነው እኛም ይህንን ለመከላከል የምናደርገው በጣም አናሳ ነው” ሲሉም ገልጸዋል።

“ሰዎችን በጨረቃ ላይ ማሳረፍ ችለናል። ሰማይ ጠቀስ ፎቆች፣ እንደ ሁቨር ያሉ ግዙፍ ግድቦችን መገንባት ብንችልም የልጆቻችን ደህንነት በትምህርት ቤቶች ውስጥ መጠበቅ አልቻልንም” ብለዋል።

አባትየው ባለፈው ወርም “ሃና የሌለችበት ዓለም እያንዳንዷ ቀን የትግል ናት “ ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

“ሁልጊዜም ትስቃለች፤ በአካባቢዋ ያሉ ሰዎችንም ታስቃለች” ሲሉም ያወሳሉ።

አቃቤ ህግ ካረን ማክዶናልድ ህይወታቸውን ካጡ አራት ታዳጊዎች ወላጆች ጋር ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተናገሩት ብያኔው “ልጆቻቸውን መልሶ ባያመጣም ተጠያቂነትን ያሳያል” ብለዋል።