የኒውዚላንድ አየር መንገድ እንደ ሻንጣ የተሳፋሪዎችን ክብደት መመዘን ጀመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኒውዚላንድ አየር መንገድ መንገደኞች አውሮፕላን ከመሳፈራቸው በፊት ልክ እንደሻንጣ ሁሉ የተሳፋሪዎችን ኪሎ መመዘን ጀመረ።
ይሁንና አየር መንገዱ ይህን ያደረገው ሰዎችን በሚመዝኑት ኪሎ መጠን ለማስከፈል አይደለም።
የተሳፋሪዎችን አማካይ የኪሎ መጠን ሚዛን ማወቅ ፈልጎ ነው ይህን እያደረገ ያለው።
የተሳፋሪዎች ክብደት ምሥጢር ሆኖ በአየር መንገዱ የመረጃ ዳታቤዝ ተሰንዶ ይቀመጣል ተብሏል።
የአየር መንገዱ ሠራተኞችም ቢሆን የመንገደኞችን ክብደት በርብረው ማግኘትና ማወቅ አይችሉም ብሏል ድርጅቱ።
'ለምን የተሳፋሪዎችን አማካይ ክብደት ማወቅ አስፈለገህ?' ተብሎ የተጠየቀው አየር መንገዱ አማካይ ሚዛናቸውን ማወቄ ለነዳጅ የቁጠባ አጠቃቀም በጣም ስለሚረዳኝ ነው ብሏል።
ከሦስት ዓመት በፊት ይኸው አየር መንገድ የአገር ውስጥ መንገደኞችን ከመሳፈራቸው በፊት ሚዛን መመዘን ጀምሮ ዜና ሆኖ ነበር።
“አሁን ዓለም አቀፍ ተጓዦችን በሚዛን ላይ እንዲቆሙ እያደረግን ነው። አሁን ተራው የነርሱ ነው” ብሏል አየር መንገዱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ።
ኮቪድ ተህዋሲ ዓለምን ከማተረማመሱ በፊት አየር መንገዱ በዓመት 17 ሚሊዮን ሰዎችን ከቦታ ቦታ አሳፍሯል።
ከኮቪድ በፊት ኒውዚላንድ አየር መንገድ በሳምንት ብቻ 3400 በረራዎችን ያደርግ ነበር።
“በአውሮፕላኑ የሚሳፈር ሰዉም ሆነ ቁስ ኪሎውን ማወቅ ደንብ ነው” ብሏል የኒውዚላንድ አየር መንገድ ቃል አቀባይ አላስቲየር ጄምስ።
መንገደኞች ሚዛኔን ሰዎች ያውቁብኛል የሚል ስጋት እንዳይገባቸው፤ ኪሏቸው በምሥጢር እንደሚጠበቅም ይኸው የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ በቪዲዮ ባሰራጨው መረጃ አረጋግጧል።
“ሚዛን ላይ መቆም እንደሚከብድ ይገባናል፥ ደንበኞቻችን እርግጠኛ መሆን ያለባቸው ማንም ክብደታቸውን ማየት እንደማይችል ነው። እኛ ክብደታቸውን የምንፈልገው ነዳጅ አጠቃቀማችን በመረጃ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ብቻ ነው” ብሏል።
ኒውዚላንድ አየር መንገድ አሁን በድምሩ የ10ሺህ ተሳፋሪዎችን ኪሎ ማወቅ ግብ አድርጎ ነው የተነሳው።
ሁሉም ተሳፋሪዎች ታዲያ ዓለም አቀፍ በረራ የሚያደርጉ መሆን አለባቸው።
ኒውዚላንድ አየር መንገድ የአገሪቱ ብሔራዊ አየር መንገድ ሲሆን 104 አውሮፕላኖች አሉት።












