በቺሊ የደን ቃጠሎ ቢያንስ 112 ሰዎችን ገደለ

ታትሟል

በቺሊ ቫልፓራሶ በተባለ ግዛት በተከሰተ የደን ቃጠሎ ቢያንስ 112 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ገብርኤል ቦሪክ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጁ ሲሆን ተጎጂዎችን ለመርዳት አስተዳደራቸው የተቻለውን ሁሉ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

በዚህ የደን ቀጠሎ ሕይወታቸውን ያጡት አብዛኛዎቹ በሽርሽር ላይ የነበሩ ጎብኚዎች ናቸው ተብሏል።

በአሁኑ ወቅት የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በቃጠሎው ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት ቦታ መድረስ እንዳልቻሉ የተገለጸ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል የአገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትር ካሮሊና ቶሃ አሳስበዋል።

ይህ በቺሊ ታሪክ በእሳት አደጋ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጋ ሕይወቱን ያጣበት ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን አደጋው በአገሪቱ የጤና ሥርዓት ላይ ጫና እንዳያሳድር ተሰግቷል።

የአገሪቱ ጤና ሚኒስቴር የመጨረሻ ዓመት የሕክምና ተማሪዎች በጊዜያዊነት ወደ ሥራ ሊያሰማራ መሆኑን እና ጊዜያዊ ሆስፒታሎችን እያቋቋመ መሆኑን አስታቋል።

በደን ቃጠሎው መኖሪያ ቤታቸው የተቃጠለባቸው አንድ አዛውንት ለፈረንሳይ የዜና ወኪል ለኤኤፍፒ ሲናገሩ አደጋውን “ገሃነም” ሲሉ የገለጹት ሲሆን በመኖሪያ አካባቢያቸው ያሉት አብዛኛዎቹ አዛውንቶች መሆናቸው ተናግረዋል።

ሮድሪጎ ፑለጋር የተባሉት የ61 ዓመቱ አዛውንት አንድ ጎረቤታቸው ዕድሜያቸው የገፋ ከመሆኑ የተነሳ ከእሳት አደጋው ማምለጥ ስላልቻሉ ሕይወታቸው አልፏል ብለዋል።

የቺሊ መንግሥት እሳቱ ከ3 እስከ 6ሺህ መኖሪያ ቤቶችን ሳያወድም እንደማይቀር ገምቷል።

እሳቱን ለመቆጣጠር 1 ሺህ 400 የእሳት አደጋ ሠራተኞች ተሰማርተዋል። የአገሪቱ ሠራዊትም የአደጋ ጊዜ ሠራተኞችን ለመደገፍ ወደ አካባቢው ተሰማርቷል።

የደን ቃጠሎውን መንስዔ ለማወቅ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጨምረው ተናግረዋል።