አርሰናል ከሲቲ ያለውን የነጥብ ልዩነት በ7 ሲያሰፋ ዩናይትድ አራተኛ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል ከማንችስተር ሲቲ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት በ7 በማስፋት የሊጉ መሪነቱን አጠናከረ።
መድፈኞቹ ወደ አሜክስ ተጉዘው ከብራይተን ጋር ተገናኝተው አዝናኝ በሆነ ጨዋታ 2 ለ 4 አሸንፈዋል።
አርሰናል ከሲቲ ጋር ያለው ልዩነት የሰፋው ሲቲ ቀደም ብሎ በተካሄደ ጨዋታ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት ከኤቨርተን ጋር 1 አቻ መለያየት ግድ ከሆነበት በኋላ ነው።
በአርሰናል እና ብራይተን ጨዋታ መድፈኞቹ ቀድመው የበላይነት በመያዝ በቡካዮ ሳካ፣ ማርቲን ኦዴጋርድ እና ኤዲ ኒኪታ 0 ለ 3 ጎሎች መምራት የቻሉ ሲሆን የማታ ማታ ባለ ሜዳዎቹ መድፈኞቹን ተፈታትነው ነበር።
ሚቶማ አንድ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው 1-3 ከሆነ በኋላ የአርሰናሉ የክንፍ ተጫዋች ገብሪኤል ማርቲኔሊ ተጨማሪ ጎል አስቆጥሩ መድፈኞቹን አረጋግቷል።
ምንም እንኳ ባለሜዳዎቹ ጨዋታው እየተጠናቀቀ 1-4 ቢመሩም እጅ የሚሰጡ አልሆኑም ነበር። ብራይተኖች በጠንካራ የማጥቃት ጨዋታ ተጨማሪ ጎል ያስቆጠሩ ሲሆን ለሦስተኛ ግዜ ኳስን ከመረብ አገናኝተው የነበረ ቢሆንም ጎል አስቆጣሪው ሚቶማ ከጨዋታው ውጪ በመሆኑ ቡድኖቹ 2-4 ተለያይተዋል።
ማንችስተር ሲቲ 1 - 1 ኤርቨተን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ያለፈው የውድድር ዓመት ሻምፒዮኖቹ ከመድፈኞቹ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ባለበት ማቆየት አልቻሉም።
ሰማያዊዎቹ ኤቨርተንን በሜዳቸው ሲያስተናግዱ የተጋጣሚያቸውን ወቅታዊ አቋም ከግምት በማስገባት ጨዋታውን በበላይን እንደሚያጠናቅቁ የብዙዎች ግምት ነበር።
በኤሪክ ሃላንድ ጎልም ሲቲዎች ቀዳሚዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ በሁለተኛው አጋማሽ የኤቨርተኑ ዲማራይ ግሬይ ያስቆጠራት ጎል ኤቨርተን ውድ የሆነች 1 ነጥብ ከሲቲ እንዲወስድ አስችላለች።
በደረጃ ሰንጠረዡ ሲቲ ከመሪው አርሰናል በ7 ነጥብ ርቆ በ36 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል
ዎልቭስ 0 - 1 ማንችስተር ዩናይትድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ማርከስ ራሽፎርድ ከተቀያሪ ወንበር ተነስቶ ለኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን ብቸኛውን ጎል በማስቆጠር ወሳኝ ሦስት ነጥብ ለቡድኑ አስገኝቷል።
ቴን ሃግ ወሳኟን ጎል ያስቆጠረላቸውን ራሽፎርድን ‘በድሲፕሊን’ ምክንያት ከቋሚ ተሰላፊነት እንዳወጡት ገልጸዋል።
ዎልቭሶች አዲሱን ዓመት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ሆነው ለመቀበል ተገደዋል።
ትናንት ቅዳሜ በተካሄዱት ሌሎች የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በርንዝማውዝ ክርስቲያል ፓላስን አስተናግዶ 2 ለ 0 ተሸንፏል።
ፉልሃም ደግሞ በአስደናቂ ግስጋሴው ቀጥሏል። ፉልሃም ሳውዝሃምፕተንን 2-1 አሸንፏል።
ኒውካስል ደግሞ ሳይገመት በሜዳው ከሊደስ ጋር ያለ ጎል ተለያይቷል።
17ኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው የሚካሄዱ ሲሆን 11 ሰዓት ሲል ቶተነሃም አስቶን ቪላን ያስተናግዳል። ማታ 1፡30 ላይ ደገሞ ቼልሲ ከኖቲንግሃም ፎርስት ጋር ይጫወታል።












