ሊሲቻንስክ ከተማ በሩሲያ እጅ መውደቋን ዩክሬን አመነች

ሊሲቻንስክ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የዩክሬን ጦር ምሥራቃዊቷን የሊሲቻንስክ ከተማን ለቆ በመውጣት በሩሲያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባቷን ዩክሬን አረጋገጠች።

“ከከባድ ውጊያ በኋላ የዩክሬን ጦር ከይዞታቸው በመልቀቅ ለማፈግፈግ ተገዷል” ብለዋል የዩክሬን ጦሩ ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም።

ቀደም ብለው የሩሲያ የመከላከያ ሚንስትር ሰርጊ ሾይጉ ሊሲቻንስክን መያዛቸውን እና የሉሃንስክ ግዛትን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን ገልጸው ነበር።

የዩክሬኑ የጦር አዛዥ በሰጡት መግለጫ “የዩክሬንን ደጀኖች ሕልውና ለመጠበቅ ሲባል ከተማዋን ለቅቀን እንድንወጣ ወስነናል” ብለዋል።

ሩሲያ በመድፍ፣ በተዋጊ አውሮፕላን፣ በሰው ኃይል እና በሌሎች ትጥቆች ብልጫ እንዳላት ይነገራል።

ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ “ምስጋና ለሚቀርብልን ዘመናዊ መሣሪያ ይሁንና የዩክሬን ጦር ወደ ሊሲቻንስክ ይመለሳል” ብለዋል።

ከእዚህም በተጨማሪ በምዕራብ አቅጣጫ በዩክሬን ቁጥጥር ሥር ያለችው ስሎቭያንስክም በከባድ መሣሪያ እየተደበደበች ነው ተብሏል። በድብደባውም ቢያንስ ስድስት ሰዎች እንደሞቱ ተነግሯል።

ከተማዋ ዶኔስክ ክልል ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ከሉሃንስክ ጋር በመሆን በኢንዱስትሪ የበለጸገችውን የዶንባስ ግዛትን ይፈጥራሉ።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጦርነት ከማወጃቸው በፊት ሉሃንስክ እና ዶኔስክ ግዛቶች ከዩክሬን ነጻ ናቸው ብለው አውጀው ነበር።

 በእነዚህ አካባቢዎች የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች ከ2014 ጀምሮ ሽምቅ ውጊያ ሲያካሂዱ ነበር። ከሳምንታት በፊት በከባድ መሣሪያ ዶጋመድ የሆነችውን ሴቨሮዶንስክን የሩሲያ ወታደሮች ተቆጣጥረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሊሲቻንስክ ከፍ ካለ መልክዓ ምድራዊ ቦታ ላይ የተገነባች ከተማ በመሆኗ ለመከላከል የተሻለ ተፈጥሯዊ ወታደራዊ ጠቀሜታ ሊኖራት ይችላል የሚል ተስፋ ነበር።

ነገር ግን የሩሲያ ኃይሎች ዙሪያውን በማጠር መውጫ መግቢያውን በመዝጋታቸው ነገሮች ለዩክሬን ጦር ቀላል ሊሆኑ አልቻሉም።

የተወሰነው የዩክሬን ጦር ከሳምንት በፊት ከከተማዋ ወጥቷል። የዩክሬን ባለሥልጣናት ባልተለመደ መልኩ በከተማዋ የሚካሄደውን ጦርነት በማስመልከት ዝምታን መርጠዋል። በይፋ ማፈግፈጋቸውን ባይገልጹም በምሥራቁ በኩል ይሄኛው ሌላኛው ከተማን ጥሎ የመውጣት ሂደት ሊሆን ይችላል። 

የሊሲቻንስክ በሩሲያ እጅ መውደቅ በምንም መስፈርት የዶንባስን ጦርነት ፍጻሜን አያሳይም። አሁንም ብዙ ከተሞችን በጎረቤት ዶኔስክ ግዛት ውስጥ ዩክሬን እንደያዘች ነች።

ምንም እንኳ በሩሲያ ከፍተኛ የከባድ መሣሪያ ጥቃት ውስጥ ቢሆኑም ዩክሬኖች ጦራቸው በባክሙት እና ስሎቭያንስክ መካከል አዲስ የመከላከል ዝግጅት እያደረገ ነው።

በሁለቱም ኃይሎች በኩል ከፍተኛ ኪሳራ ደርሷል። ጥያቄው ግን ዩክሬን የሩሲያን ወረራ ትገታለች ወይስ ሩሲያ ወደፊት መገስገሷን ትቀጥላለች የሚለው ነው። ስሎቪያንስክ እና ክራማቶርስክ አሁንም በዩክሬን እጅ ውስጥ የሚገኙ ትልልቅ የዶኔስክ ክልል ከተሞች ናቸው።

የሩሲያ ጦር በስሎቪያንሰክ ከተማ ላይ ከባድ መሣሪያዎችን እየተኮሰ ሲሆን እሁድ ዕለት 15 ከባድ መሣሪያዎች ወደ ከተማዋ መተኮሳቸውን የከተማዋ ከንቲባ ገልጸዋል። በቅርብ ጊዜ ወደ ከተማዋ ከሚተኮሰው ከባድ መሣሪያ ይህኛው የከፋው መሆኑንም ተናግረዋል።

ትዊትር ላይ የሚዘዋወረው የፍንዳታ ምስልም ይህንን ያረጋግጣል። በቀድሞው የፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ቃል አቀባይ የተጋራ ነው።

በሌላ በኩል በሰሜን አቅጣጫ ከዩክሬን ድንበር 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቤልጎሮድ ከተማ ላይ ዩክሬን ሲቪሎችን ኢላማ ያደረገ የሚሳኤል ጥቃት እየፈጸመች መሆኑን ሩሲያ ከሳለች። በጥቃቱም 4 ሰዎች መሞታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣን ተናግረዋል።

የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ደግሞ ሦስት የዩክሬን ሚሳኤሎች ተመትተው መውደቃቸውን፣ ነገር ግን ስብርባሪው በአፓርትመንት ላይ አርፎ ጉዳት ማድረሱን ገልጿል።

ዩክሬን በበኩሏ ጥቃቱን እንዳልፈጸመች በመግለጽ ትንኮሳ እየተፈጸብኝ ነው ብላለች።