የሁለት ዓመቷ አሜሪካዊት 'ያለምንም ምክንያት' ተጠርዛ ወደ ሆንዱራስ ሳትላክ እንዳልቀረች ተገለጸ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የአሜሪካ ዜግነት ያላት የሁለት ዓመት ሕጻን ከእናቷ እና ከ11 ዓመት እህቷ ጋር ያለምንም ትርጉም ያለው የሕግ ሂደት ወደ ሆንዱራንስ ተጠርዛ ተልካ ሊሆን እንደሚችል የፌዴራል ዳኛ ተናገሩ።

ይህ የተሰማው የፕሬዚደንት ትራምፕ አስተዳደር ሕገ ወጥ ያላቸውን ስደተኞች ወደ አገራቸው ማባረሩን አጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት ነው።

ዳኛ ቴሪ ዳውቲይ እንዳሉት 'ቪኤምኤል' በሚል መለያ የምትጠራው ሕጻን ያለምንም ትርጉም ያለው የሕግ ሂደት ተጠርዛ ተልካ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ጥርጣሬ አለ።

በሉዚያና የተወለደችው ሕጻኗ እና የቤተሰብ አባላቶቿ ከአምስት ቀናት በፊት በኒው ኦርሊያንስ የኢሚግሬሽን ቢሮ ላይ እንደተያዙ ሰነዶች ጠቁመዋል።

የአገር ውስጥ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ በበኩላቸው እናትየዋ ወደ ሆንዱራንስ ስትላክ ልጆቿን ይዛ መሄድ እንደፈለገች ተናግረዋል።

የፍርድ ቤቱ ሰነድ እንደሚያመለክተው ዳኛው ከሕጻኗ እናት ጋር በስልክ ለመነጋገር ማመቻቸት ፈልገው በጠየቁበት ወቅት እናትና ልጅ ወደ ሆንዱራንስ በመላካቸው ማነጋገር እንደማይችሉ በመንግሥት ጠበቃ ተነግሯቸዋል።

የሕጻኗ እናት፣ አባት እና እህት የኢሚግሬሽን ሁኔታ ግልጽ አይደለም።የሁለት ዓመቷ ሕጻን ግን የአሜሪካ ዜጋ ናት።

በመሆኑም " የአሜሪካ ዜጋን ጠርዞ መላክ፣ ለማባረር ማሰር ወይም ከአገር እንዲወጣ ማዘዝ ሕገ ወጥ እንዲሁም ሕገ መንግሥቱን የሚጻረር ነው" ብለዋል ዳኛው።

ዳኛው ጨምረውም "ያለ ምንም ምክንያት መንግሥት የአገሪቷን ዜጋ ሳያባርር እንዳልቀረ ያለውን ጥርጣሬ ለማጥራት" ለአውሮፓውያኑ ግንቦት 19 ቀጠሮ መሰጠቱን ተናግረዋል።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ኒውስ በተላከ መግለጫ ላይ የአገር ውስጥ ደኅንነት ረዳት ጸሐፊ ትሪሲያ ማክላግሊን እንዳሉት ሕጻኗ የተወሰደችው በቤተሰቦቿ ውሳኔ ነው ።

" ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር መጠረዝን መምረጣቸው የተለመደ ነው" ብለዋል።

በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሕጻኗ አባት ሕጋዊ የማሳደግ ሥልጣኑን በጊዜያዊነት ለማስተላለፍ ማመልከቻ አስገብቶ ነበር። ይህም በግዛቲቱ ሕግ መሠረት የአሜሪካ ዜግነት ያላት የሚስቱን እህት የልጆቹን የማሳደግ መብት የሚሰጥ ነው።

ሆኖም የኢሚግሬሽን እና ጉምሩክ መሥሪያ ቤት ወኪል አባትየው ልጅቷን ሊያመጣት እንደሚችል፤ ነገር ግን እርሱ ሊታሰር እንደሚችል በመግለጽ ጥያቄውን እንደማይቀበለው ለቤተሰቡ ጠበቃ አሳውቋል።

በሌላ ተመሳሳይ ጉዳይም ባለቤቷ የአሜሪካ ዜግነት ያለው ኩባዊት ከአንድ ዓመት ልጇ ጋር በኢሚግሬሽን ቀጠሮ ወቅት ታስረው፤ ከሁለት ቀናት በኋላ ወደ ኩባ እንዲመለሱ መደረጋቸውን መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ሄዲይ ሳንቺዝ የተባለችውና በሚጥል በሽታ የምትሰቃየው እናት ልጇን ጡት እያጠባች እንደነበር ጠበቃዋ ገልጸዋል። ጠበቃው ጨምረውም ሂዲይ ወንጀለኛ እንዳልሆነችና ከሰብዓዊ ጉዳይ ጋር በተያያዘ በአሜሪካ መቆየት እንደነበረባት ተናግረዋል።

ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጥር ወር መጀመሪያ ላይ ወደ መንበረ ሥልጣን ከመጡ ወዲህ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ ስደተኞች ታስረዋል።

ትራምፕ ባላቸው ጥብቅ የስደተኞች ፖሊሲ በርካታ የሕግ መሠናክሎች አጋጥመዋል።

ከዚህ ቀደም መንግሥት የኤል ሳልቫዶር ዜግነት ያለውን ኪልማር አብሪጎ ጋርሺያ በስህተት ማባረሩን አምኗል። ሆኖም ግለሰቡ የኤምኤስ -13 የወንበዴ ቡድን አባል በመሆኑ ወደ አሜሪካ እንደማይመለስ የገለጸ ሲሆን የአብሪጎ ጠበቃ እና ቤተሰቦች ግን የቀረበውን ክስ ውድቅ አድርገውታል። አብሪጎ በምንም ዓይነት ወንጀል ተከሶ አያውቅም።

ጠቅላይ ፍርድ ቤትም መንግሥት አብሪጎን የሚመለስበትን ሁኔታ እንዲያመቻች የወሰነ ቢሆንም፤ የትራምፕ አስተዳደር ግን አብሪጎ ከዚህ በኋላ 'በፍጹም' በአሜሪካ አይኖርም ብሏል።