ግብፅ በተመድ የሰላም አስከባሪ ኃይል ሥር በማሊ ያለኝን ተሳትፎ አግጃለሁ አለች

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ግብፅ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይል ሥር በማሊ ውስጥ ያሰመራቻቸው ወታደሮቿን ተሳትፎ ማቋረጧን አስታወቀች።
ግብፅ ከዛሬ ሰኞ ነሐሴ 09/2014 ዓ.ም. ጀምሮ ወታደሮቼ በማሊ ሰላም አስከባሪ ኃይል ሥር የሚኖራቸው ተሳትፎ የሚቋረጠው በአገሪቱ ውስጥ በደኅንነት ስጋት ምክንያት ነው ብላለች።
በማሊ ተሰማርተው ከሚገኙ የግብፅ ወታደሮች መካከል ስምንቱ ባለፉት ስምንት ወራት በታጣቂዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
ከግብፅ በተጨማሪ ጀርመን የአየር በረራ ፍቃድ ከተከለከለች በኋላ በማሊ የነበራትን ወታደራዊ ተልዕኮ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቋረጥ አድርጋለች።
ሚያዚያ 2014 ዓ.ም. ላይ ከ10 አገራት የተወጣጡ የጦር ኃይል አባላት ‘ሚኒሱማ’ ተብሎ በሚጠራው ጦር ውስጥ የሰላም ማስከበር ሥር ላይ ተሰማርተው ይገኙ ነበር።
ናይሮቢ ኬንያ የሚገኘው የግብፅ የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ (ሚሽን) በማሊ ሚኒሱማ ውስጥ ተሰማርቶ የሚገኘው ወታደራዊ ኃይሏ ከአገሪቱ ለቆ እንደሚወጣ ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህ እርምጃ ለምን ያህል ጊዜ ተግባራዊ እንደሚቆይ የተባለ ነገር ለም።
ግብፅ በማሊ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ውስጥ በአብዛኛው በሎጂስቲክ ሥራ ላይ የተሰማሩ 1000 ሺህ ወታደሮች አሏት።
ይህ የግብፅ ውሳኔ የተሰማው በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘው ወታደራዊው መንግሥት አዲስ የተባበሩት መንግሥታት ወታደሮችን ወደ ማሊ እንዲገቡ ከፈቀደ በኋላ ነው።
ወታደራዊው መንግሥት ከአይቮሪ ኮስት ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ መግባቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት የሰላም አስከባሪ ኃይል ስምሪትን ከሳምንታት በፊት አቋርጦ ነበር።
ማሊ 49 የአይቮ ኮስት ወታደሮችን “ከብሔራዊ ደኅንነት” ጋር በተያያዘ ስጋት አለኝ በሚል በቁጥጥር ሥር ማዋሏን ተከትሎ በሁለቱ የምዕራብ አፍሪካ አገራት መካከል ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።
ወታደሮቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት እሁድ ሐምሌ 03/2014 ዓ.ም. በማሊ መዲና ባማኮ አየር ማረፊያ ሲሆን፣ የአገሪቱ ወታደራዊ መንግሥት ወታደሮቹ ቅጥረኛ ወታደሮች ናቸው ብሎ ነበር።
የአይቮሪ ኮስት መንግሥት በበኩሉ ወታደሮቹ በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት አንዳቸውም የጦር መሳሪያ ታጥቀው እንዳልነበረ እና ወደ ማሊ የተጓዙት የተባበሩት መንግሥት ሰላም አስከባሪ ኃይል ተልዕኮ አካል ሆነው ነው ብሏል።
በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የያዘው የማሊ ወታደራዊ መንግሥት ከጎረቤት አገራት እና ከምዕራባውያን ጋር ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ ይገኛል።
በምትኩም ወታደራዊው መንግሥት ከሩሲያ ጋር ያለውን ወዳጅነት እያጠናከረ ነው። ማሊ ከሩሲያ የተረከበቻቸውን በርካታ ተዋጊ አውሮፕላኖችን በዋና ከተማዋ ባማኮ አየር ማረፊያ ለዕይታ አቅርባ ነበር።












