ፈረንሳይ ጦሯን ማስወጣቷን ካስታወቀች በኋላ የማሊ ወታደሮች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በሰሜናዊ ምሥራቃዊ አርካም ክልል አማፂያን ባደረሱት ጥቃት ስምንት ወታደሮቹ መገደላቸውን እና አምስቱ እንደጠፉ የማሊ ጦር አስታወቀ።
ግጭቱ የተከሰተው ፈረንሳይ እና አጋሮቿ ጦራቸውን ከማሊ እናስወጣለን ካሉ ከቀናት በኋላ ነው።
ከሰሞኑ ለተፈፀመው ጥቃት ምላሽም የማሊ አየር ኃይል 57 ታጣቂዎችን መግደሉን ጦሩ በመግለጫው አክሏል።
ወታደሮቹ የአማፂያን መደበቂያ ቦታዎችን ሲያፈነፍኑ በነበረበት ወቅት "ማንነታቸው ባልታወቁ የታጠቁ ሰዎች" እንደተተኮሰባቸውና እንደሞቱም ተነግሯል።
የፈረንሳይ ወታደሮች ከአገሪቱ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ እንዲሁም በቀጠናው የሩሲያ ቅጥረኞች መሰማራት በማሊ የጸጥታ ሁኔታ ላይ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ስጋት ጭሯል።
በዚህ ሳምንት ብቻ፣ እስላማዊ መንግሥትን ጨምሮ ተቀናቃኝ እስላማዊ ቡድኖች በሚንቀሳቀሱበት አርካም ክልል 40 ንፁሀን ዜጎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።
ማሊ ለዓመታት ከጂሃዲስቶች ጋር ስትታገል ቆይታለች። ከዚህ ጋር ተያይዞም በአውሮፓውያኑ 2020 ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ቡባካር ኬይታ ከፍተኛ ተቃውሞ የተነሳባቸው ሲሆን ይህንንም ተከትሎ የአገሪቱን ጸጥታ እናስከብራለን በሚልም መፈንቅለ መንግሥት ተካሂዶባቸዋል።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሃገሪቱ አዲስ ወታደራዊ አመራሮች ከቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ጋር አለመግባባቶች ተፈጥሯል።
በዚህ አመት ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድ የተደረሰውን ስምምነት በመሻር እና የፈረንሳይ አምባሳደርም ሲቃወሙ ማባረራቸው ይታወሳል።
ጂሃዲስቶችን ለ10 ዓመታት ያህል ስትዋጋ የነበረችውን ፈረንሣይ ሁሉንም ወታደሮቿን እንድታስወጣ ማሊ ትዕዛዝ ሰጥታለች።
በሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ወታደሮች የተጠናከረው የማሊ ጥምር ተልዕኮ ወይም ታኩባ ግብረ ሃይል በአሁኑ ወቅት ድንበሩን አቋርጦ ወደ ኒጀር በመጓዝ አሁን ካለው የጦር ሰፈር በቅርብ ርቀት ላይ ሆኖ ይቆያል።
የኒጀር ፕሬዝዳንት አርብ ዕለት እንዳሉት የፈረንሳይ ጦር እና አጋሮቻቸው ከማሊ መውጣታቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ድንበሮች ለጂሃዲስት ታጣቂዎች እንቅስቃሴ የበለጠ ተጋላጭ ይሆናሉ።
በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ የኒጀር ፕሬዚዳንትና ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ መሪዎች የፈረንሳይ ጦር ከማሊ መውጣቱን በተመለከተ ይፋ ከማድረጉ በፊት ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጋር የተገናኙ ሲሆን ሲሆን በውይይታቸውም ወታደሮቹ ወደ ቀጣናው ሀገራት እንዲዘዋወሩ ተስማምተዋል።












