አንዲት ፖሊስን በከንፈር እንቅስቃሴ ብቻ ‘እርጂኝ’ ብላ ከአጋቿ ነጻ የወጣችው ሴት

የፎቶው ባለመብት, NORTH MYRTLE BEACH POLICE DEPARTMENT
በአሜሪካ፣ ሳውዝ ካሮላይና አንዲት ሴት ካገታት ሰው ጋር መኪና ውስጥ ሳለች ፖሊስ ደርሳ አትርፋታለች።
የታገተችው ሴት መኪና ውስጥ ሳለች መኪናው ቀይ መብራት ጥሶ ያልፋል።
መኪናው ቀይ መብራት ጥሶ በማለፉ ካይላ ዋልስ የተባለች ፖሊስ መኪናውን ታስቆማለች።
በዚህ ወቅት ነው መኪና ውስጥ ያለችው ሴት ለፖሊሷ “እርጂኝ” የሚል ምልክት የሰጠቻት።
ታጋቿ ድምጽ ሳታሰማ ከንፈሯን በማንቀሳቀስ ብቻ ፓሊሷን ደጋግማ “እርጂኝ” እያለቻት ነበር።
መኪናውን እየነዳች የነበረችው ታጋቿ ነበረች። አጠገቧ ያለው አጋች ከተኩስ ልውውጥ በኋላ በመሣሪያ አስፈራርቶ እንዳገታት ተገልጿል።
ተጠርጣሪው ኪሊንስ ቤትስ የተባለ የ29 ዓመት ሰው ሲሆን በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ፖሊሷ መኪናው ቀይ መብራት ጥሶ እስክታቆመው ድረስ በአቅራቢያው ተኩስ መከፈቱን እንዳላወቀች የቢቢሲ የአሜሪካ አጋር ሲቢኤስ የኖርዝ ማርትል ቢች ፖሊስ ኃላፊ ፓት ዊኒንሰንን ጠቅሶ ዘግቧል።
ፖሊሷ ካይላ ዋልስ ከሥራ ልትወጣ 30 ደቂቃ ብቻ ነበር የቀራት።
መኪናውን አስቁማ አሽከርካሪዋ ከመኪናው ስትወርድ ጭንቀት ውስጥ እንዳለች ተረዳች።
“የመኪናውን በር እንድትዘጋው ትዕዛዝ ሰጠሁ። ከጎኗ የነበረው ተሳፋሪም በሩን ከፍቶ መስኮቱን መክፍት እንዳልቻለ ተናገረ” ብላለች ፖሊሷ።
“አሽከርካሪዋ ሊያስመልሳት እንደሆነ ነገረችኝ” ስትልም አክላለች።
ከጎኗ የነበረው አጋች ሳያያት ለፖሊሷ ደጋግማ “እርጂኝ” እያለች ምልክት ታሳይ ነበር።
አጋቹን መኪናዋ ውስጥ ካስገባች በኋላ አሽከርካሪዋን ስታዋራት ምን እንደተከሰተ ማወቅ ችላለች።
ግለሰቡ ሰው ላይ ተኩሶ አሽከርካሪዋን በመሣሪያ አስገድዶ በመኪናዋ እንድትወስደው እንዳደረገ ለፖሊሷ ነገረቻት።
ፖሊሷ መኪናውን ባስቆመችበት ቅጽበት ተጠርጣሪው በመንገዱ ሊያልፍ ስለሚችል ጥበቃ እንዲደረግ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።
ተኩስ በአካባቢው ተከፍቶ ነጭ ጂፕ መኪና እንደተሰወረ ከተገለጸ በኋላ ነው ክስተቱ የተፈጠረው።
በተላለፈው ትዕዛዝ የተጠቀሰው ግለሰብ መኪና ውስጥ ከነበረው ተሳፋሪ ጋር ተመሳሳይ ነበር።
ተጨማሪ ፖሊሶች ተጠርተውም በቁጥጥር ሥር ውሏል።
በግድያ ሙከራ፣ በእገታ እና መሣሪያ ይዞ ወንጀል በተፈጸመበት ቦታ በመገኘት ክስ ይመሠረትበታል።
መኪና ውስጥ ደብቆት የነበረው መሣሪያ ተይዟል።
የፖሊስ ክፍሉ “ፖሊሷ የኛ ክፍል ባልደረባ በመሆኗ ኩራት ይሰማናል” ብሏል።












