የትዊተር ተጠቃሚዎች ኤሎን መስክ በኃላፊነት እንዳይቀጥል ድምጽ ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ቢሊዮነሩ ኤሎን መስክ በትዊተር ዋና ስራ አስፈጻሚነቱ ለመቀጠል ወይም ላለመቀጠል በማህበራዊ ገጹ አማካኝነት ያሰባሰበው ድምጽ ሃላፊነቱን እንዲለቅ የሚደግፍ ሆኗል።
120 ሚሊዮን ተካታዮች ያሉት መስክ “ሃላፊነት ብለቅ ይሻላል ወይ?” ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄዎች 57.5 በመቶው “አዎ” የሚል ድምጽ ሰጥተዋል።
በ44 ቢሊዮን ዶላር ትዊተርን የገዛው ባለሃብቱ ቀድም ብሎ ለውጤቱ ተገዢ እንደሚሆን ገልጾ ነበር።
የቴስላ እና የስፔስ ኤክስ የሚመራው መስክ ትዊተርን ለማስተዳደር ሲረከብ ከፍተኛ ትችት ደርሶበት ነበር።
የድምጽ መስጫ ጊዜው ከበቃ በኃላ ቢሊየነሩ የሰጠው አስተያየት የለም። የትዊተር ስራ አስፈጻሚ ሆኖ ይቀጥላል ወይስ አይቀጥልም የሚለው ላይ እንኳን የተናገረው ነገር የለም።
ከተከታዮቹ 17.5 ሚሊዮኖቹ ድምጽ የሰጡ ሲሆን 42.5 በመቶ የሚሆኑት መስክ ሃላፊ ሆኖ ይቀጥል ብለዋል።
ባለሃብቱ ከዚህ በፊት ለትዊር ድምጽ ውጤቶች ተገዢ ሆነው ታይተዋል። “የህዝቦች ድምጽ የፈጣሪ ደምጽ ነው” የሚል ግርድፍ ትርጉም ያለውን የላቲኖች አባባልን መጠቀስ ይወዳል።
በቅርቡ ከስራው የለቀቀ የትዊተር ባልደረባ ለቢቢሲ በሰጠው አስተያየት መስክ “ሁላችንም የምናውቀውን ብቃት አልባነቱን እና ሞኝነቱን እያሳየ ነው” ብሏል።
ስሜ አይጠቀስ ያለው ይህ ግለሰብ ጨምሮም “ትዊተር ላይ ኢንቨስት እያደረጉ ያሉ ሰዎች የሱን ትክክለኛ መሪነት ጥያቄ ውስጥ እያስገቡ ነው። በስልጣን እንዲለቅ በኢንቬስተሮቹ ግፊት እየተደረገበት ያለ ይመስለኛል። ስለዚህ በትዊተር በተሰጠ ድምጽ ከሃላፊነቱ እንደተነሳ ለማስመስል የሚሞክር ይመስላል” ብሏል።
የድምጽ መስጫው ጊዜ በተጠናቀቀ በደቂቃዎች ውስጥ ክሪፕቶ ላይ የሚሰራው እና ከትዊተር ኢንቨስተሮች አንዱ የሆነው ቻንግፔን ዛሆ ኤሎን መስክ ከትዊተር ሃላፊነት መውረድ የለበትም ብለዋል።
ሰውዬው መስክ ትዊተርን መረከባቸውን ደግፈው 500 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አደርገዋል።
መስክን ከሚደግፉት ሰዎች መካከል አፕል እና ጉግል ጨምሮ በርካታ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችን የሚደግፈው ተቋም ይገኝበታል።
የዓለም ዋንጫን ካስተናገደችው ኳታር ባለፈው ዕሁድ በፍጻሜ ጨዋታው ከዶናልድ ትራምፕ ልጅ ጋር የተነሱት ፎቶ ከታየ በኃላ የመስክ የግል ጀት ሲመለስ ተስተውሏል።
ዳን ኢቨስ የተባሉ ከፍተኛ ተንታኝ ለቢቢሲ የመስክን ሃላፊነት በተመለከተ የሚሰጠው ደምጽ ከመጠናቀቁ በፊት እንደተናገሩት የሚሰጠው ድምጽ የመስክን የትዊተር የስራ ዘመን ሚያጠናቀቅ ነው። ይህንንም ተከትሎ መስክ በቀታዮቹ 24 ሰኣት አዲስ ጊዜያዊ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሊሆሾሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
መስክ የትዊተርን ሃላፊነት ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ አወዛጋቢ የሆኑ ለውጦች ተካሂደዋል።
ግማሽ የሚሆነው የትዊተር ሰራተኛ ያሰናበተ ሲሆን ለሰማያዊ መረጋገጫ ክፍያ እንዲፈጸም ሙከራ እያደረገ ነው።
በሌላ በኩል መስክ የይዘት ቁጥጥር ላይ ያለው አመለካከት ላይም ሲተች ነበር። መስክ ሃሰተኛ እና የጥላቻ ይዘቶችን ሊያበርካት የሚችል እርምጃ ወስዷል በሚል ይወቀሳል።
መስክ ባለፈው አርብ ትዊተር ማህበራዊ ሚዲያው ላይ የሚሰሩ የተወሰኑ ጋዜጠኞችን በጊዜያዊነት ማገዱን ተከትሎ ከአውሮፓ ህብረት እና ከተመንግስታቱ ደርጀት ውግዘት ደርሶበታል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሚዲያ ነጻነት “መጫወቻ” አይደለም የሚል ትዊተር ሲያሰፍር የአውሮፓ ህብረት ደግሞ ትዊተር ላይ ማዕቀብ ሊጥል እንደሚችል ዝቷል።
ባለሃብቱ ድምጽ መስጠቱ ከተጀመረ በኃላ በትዊተር ገጹ “የምትመኙትን ነገር ልታገኙት ስለምትችሉ ተጠንቀቁ” ሲል ጽፎ ነበር።
ቀጥሎም “ስልጣን የሚፈልጉ ሰዎች ስልጣን የማይገባቸው ናቸው” ሲል ትዊት አድርጓል።
ከዚያም ትዊተር ላይ ታላላቅ ለውጥ ማድረግን በተመለከተ ድምጽ እንደሚሰጥ ጽፏል።












