በኳታር ሰው ሲማታ የታየው ሳሙኤል ኤቶ ይቅርታ ጠየቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ካሜሩናዊው የቀድሞው የባርሴሎና እና የብሔራዊ ቡድኑ ፈርጥ ሳሙኤል ኤቶ በኳታር ከአንድ ግለሰብ ጋር ተፈጠረ ያለውን ''ግጭት'' ተከትሎ በእርሱ በኩል ላሳየው ባህሪ ይቅርታ ጠየቀ።
በአሁን ወቅት የአገሩ ካሜሩን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት የሆነው የ41 ዓመቱ ኤቶ አንድን ግለሰብ ሲማታ የሚያሳየው ቪዲዮ በማሕበራዊ ሚዲያ ላይ መጋራቱ እና መነጋገሪያ መሆኑ ይታወሳል።
ተንቀሳቃሽ ምስሉ ክስተቱ ከማጋጠሙ በፊት ኤቶ ከአድናቂዎቹ ጋር ፎቶግራፍ ሲነሳ እና በኤቶ የተደበደበው ግለሰብ ኤቶን እየተከታተለ ሲቀርጸው ያሳያል።
ኤቶ እየተከታተለ ቪዲዮ ሲቀርጸው ከነበረው ግለሰብ ጋር የቃላት ልውውጥ ሲያደርግ ይታያል።
ሳሙኤል ኤቶ በመጀመሪያ ግለሰቡን ለመማታት ሲሞክር አጠገቡ በነበሩ ሰዎች ቢገታም፣ በድጋሚ በኃይል ይዘውት የነበሩ ሰዎችን በማስለቀቅ በእግሩ የግለሰቡን አገጭ በመማታት ጥሎታል።
ከብራዚል እና ከደቡብ ኮሪያ ጨዋታ በኋላ 974 በተሰኘው ስታዲዮም ነበር ግጭቱ የተከሰተው።
ኤቶ በቲዊተር ገፁ ላይ ባጋራው መግለጫ “በንዴት ከእኔ ማንነት ጋር የማይሄድ ምላሽ ስለሰጠሁ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብሏል። አክሎም ለዚህ አሳዛኝ ክስተት ሕዝቡን ይቅርታ እንደሚጠይቅ ተናገሯል።
ለአራት ግዜያት የአፍሪካ ምርጥ ተጫዋች ሆኖ የተመረጠው ኤቶ እንዳለው ከሆነ ባለፈው መጋቢት ወር ካሜሩን አልጄሪያን ማሸነፏን ተከትሎ ከፍተኛ ትንኮሳ እየደረሰበት እንደሆነ እና አሁን ወደግጭት የገበውም የአልጄሪያ ደጋፊ የሆነው ግለሰብ ስላስቆጣው መሆኑን ተናግሯል።
"በአንዳንድ የአልጄሪያ ደጋፊዎች የሚደርስብንን የማያቋርጥ የዕለት ተዕለት ትንኮሳ እቃወማለሁ" ሲል ኤቶ በመግለጫው አክሏል።
"በእርግጥም ከካሜሩን-አልጄሪያ ግጥሚያ ጀምሮ ያለ ምንም ማስረጃ የማጭበርበር ክስ እና ስድብ ዒላማ ሆኛለሁ'' ብሏል።
"በዚህ የአለም ዋንጫ ወቅትም ካሜሩናዊያን ደጋፊዎች በተመሳሳይ በአልጄሪያውያን ትንኮሳ እና እንግልት ደርሶባቸዋል" ብሏል።
ሳሙኤል ኤቶ በተጫዋች ዘመኑ ስኬታማ ጊዜን አሳልፏል።ለአገሩ ብሔራዊ ቡድን 118 ጊዜ ተሰልፎ 56 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ከባርሴሎና በተጨማሪ ለሪያል ማድሪድ፣ ለማሎርካ፣ ለኢንተር ሚላን፣ ለቼልሲ እና ለኤቨርተን ተጫውቷል።












