ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የብሪታንያ አየር መንገድ ከ10 ሺህ በላይ በረራዎችን ሊሰርዝ ነው
የብሪታንያ አየር መንገድ 10 ሺህ 300 አጫጭር በረራዎችን ሊሰርዝ መሆኑን አስታወቀ።
አየር መንገዱ ይህንን የሚያደርገው ከነሐሴ እስከ ጥቅምት መጨረሻ ባለው በሚያደርገው የማሻሻያ ፕሮግራም ምክንያት ነው።
ይህ ማለት በዚህ ዓመት ከሚያዚያ እስከ ጥቅምት ባለው ጊዜ ብቻ ከ30 ሺህ በላይ በረራዎች ይሰርዛሉ ማለት ነው።
የበረራ ስረዛው በርካታ ተቋማት ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል።
ኢንዱስትሪው በኮሮናቫይረስ ምክንያት ተጥሎ የነበረው እገዳ ከተነሳ በኋላ የአየር ጉዞ ፍላጎት በመጨመሩ በሠራተኛ እጥረት ተቸግሯል።
የብሪታንያ አየር መንገድ የበረራ ስረዛውን በተመለከተ በሰጠው መግለጫ፣“ሁሉም የአቪዬሽን ኢንደስትሪው በከፍተኛ ተግዳሮቶች ውስጥ እያለፈ ነው። እኛም ደንበኞቻችን የሚገባቸውን አገልግሎት ለመስጠት እየሰራን ነው” ብሏል።
በቅርቡ የተደረገውን የበረራ ስረዛ በተመለከተም የአየር መንገዱ ደንበኛ የሆኑት ሮሪ ቦላንድ፣ የብሪታንያ አየር መንገድ የክረምት በረራውን ለማድረግ አለመቻሉ “ትልቅ ስህተት” ብሎታል።
“ምንም እንኳን በቅርብ ሳምንታት በሺዎች የሚቆጠሩ ደንበኞች ጉዟቸው እየተሰረዘ ቢቸገሩም፣ አየር መንገዱ የማያሟላቸውን የበረራ ማስታወቂያዎችን መስራቱን ቀጥሏል” ብሏል ሮሪ።
ይህ የሚደረገው በረራ በቀረበበት ወቅት የሚደረግን የጉዞ ስረዛ እና መስተጓጎል ለማስቀረት ነው።
ቀድሞ በረራን መሰረዝ፣ ተጓዦች ሌላ አየር መንገድ እንዲጠቀሙ እና የከፈሉትን ገንዘብ ለማስመለስ ዕድል ይሰጣል። የተጓዦችን መስተጓጎልም ያስቀራል የሚል እሳቤ አለ። ሆኖም አሁንም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከፍተኛ እንግልት እየደረሰባቸው ነው።
የብሪቲሽ አየር መንገድ ይህ የደንበኞች መስተጓጎል የመጨረሻ ሊሆን እንደሚችል ያምናል።
ብዙዎቹ አገልግሎቶቹ አሁንም በዕቅዳቸው መሰረት እንደሚቀጥሉ አየር መንገዱ ገልጿል። ቢሆንም ግን ከኮሮናቫይረስ በኋላ ዓለም አቀፍ በረራ ለመጀመር ከሠራተኛ እጥረት ጋር ተዳምሮ ይህንን ፈታኝ እንደሚያደርገው ይገመታል።
አየር መንገዱ በሰጠው መግለጫ ላይ፣ የበረራ ስረዛው ረጅም ርቀት በረራዎችን እንደማያካትት የገለጸ ሲሆን በክረምቱ የበረራ ማስተካከያ እና ስረዛ በብዛት የሚጎዱት የአጭር ርቀት በረራዎች ናቸው ብሏል።