ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በዩክሬን ጦርነት የተገደሉባቸውን ቤተሰቦች "ከሞት ለማስነሳት" ኤአይ እየተጠቀሙ ያሉት ሩሲያውያን
በበረዶ የተሸፈነ የሞስኮ ጎዳናን በሚያሳየው ቪዲዮ ላይ የተቀነባበረ ሙዚቃ ይሰማል።
በጎዳናው ላይ የዩክሬን ጦርነት ማብቃቱን የሚያበስሩ የመልዕክት ሰሌዳዎች (ቢልቦርዶች) ተሰቅለው ይታያሉ።
"ልዩ የሆነው ወታደራዊ ዘመቻ ተጠናቋል" ይላል አንደኛው ቢልቦርድ። ክሬሚሊን በዩክሬን ለምታካሂደው ጦርነት የምትጠቀምበትን ቃል በመጠቀምም "ጀግኖቻችን ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው" ሲል ይቀጥላል።
ከዚያም አንዲት የተጨነቀች የምትመስል ቆንጆ ሴት የወታደር ልብስ የለበሰ ሰው ካየች በኋላ በእምባ ታጅባ ስትጠመጠምበት ያሳያል።
ይህ የ15 ሴኮንዶች ርዝማኔ ያለው በኤአይ የተሰራ ቪዲዮ ካትያና ጂን በሚል ስም በምትታወቀው ታዋቂዋ ጦማሪ ነበር በኢንስታግራም የተጋራው።
በቪዲዮው ላይ የሚታዩት ጥንዶች ባል እና ሚስት ይመስላሉ።
ልክ በእውነታው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮች ሁሉ እርሱም በጦር ግንባር ደብዛው ጠፍቷል። እጣ ፈንታውም አይታወቅም።
በኤአይ የተሰሩ የሩሲያ ወታደሮችን የሚያሳዩ ፎቶዎች እና ቪዲዮዎች ከአውሮፓውያኑ 2025 አጋማሽ ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያ ዝነኛ ሆነዋል።
በአብዛኛው ምሥሎቹ የሚጋሩት በዩክሬን በሚዋጉ ወታደሮች ቤተሰብ እና ዘመድ አዝማዶች ነው።
ሁሉም ለማለት በሚቻል መልኩ ወታደሮቹ የተሳሉት አገራቸውን እና የሚወዷቸውን ሰዎች ከጥቃት ለመከላከል እንደሚፋለሙ ጀግኖች ነው።
በሩሲያ ወረራ ምክንያት በዩክሬን ላይ የደረሰው ጉዳት ግን በእነዚህ ምሥሎች ላይ አይታይም። ይህም ቪዲዮውን ያዩትን በርካታ ዩክሬናውያንን አስቆጥቷል።
ምንም እንኳን በሃዘን ላይ ላሉ ቤተሰቦች የኤአይ ይዘቶች የሚወዷቸው ሰዎችን በማጣታቸው የተሰማቸውን ሃዘን ለመግለጽ መንገድ ቢሆናቸውም በአንዳንድ ሁኔታዎች በቀብር ሥፍራዎች የሞቱ ሰዎችን ምሥልም አሳይተዋል።
እንዲህ ዓይነት ምሥሎችን በተመለከተ ያለው አስተያየት የተለያየ ነው።
አንዳንዶች እንዳሳዘናቸው ሲገልጹ ሌሎች ደግሞ "ከሥነ ምግባር ያፈነገጠ እና የሚረብሽ" ብለውታል።
በኬምብሪጅ ዩኒቨርሲቲ ኤአይ ወደፊት የሚፈጥራቸው ተግዳሮቶች እና ዕድሎች ላይ ጥናት የሚያካሂደው ማዕከል ተመራማሪ የሆኑት ካታርዝይና ኖዋዚይክ ባሲንስካ፣ ቴክኖሎጂው ሃዘንን በመወጣት ሒደት ወደፊት የሚያስከትለው ሥነ ልቦናዊ እና ማኅበራዊ ቀውስ አይታወቅም ይላሉ።
"የሞቱ የሩሲያ ወታደሮችን ወይም ከዩክሬን የተመለሱ የሞቱ የሩሲያ ወታደሮችን 'ዲፕፌክ' መፍጠር እጅግ ውስብስብ እና በሥነ ምግባር ረገድ ግልጽ በሆነ መንገድ ለመገምገም አስቸጋሪ ነው" ብለዋል።
ቢቢሲ ሩሲያ ቪዲዮውን ያጋራችውን ካትያ ጂንን አስተያየት የጠየቀ ቢሆንም ምላሽ አላገኘም።
በአጋጣሚ ይሁን አይሁን ባይታወቅም ታሪኩ መጀመሪያ ላይ በቢቢሲ ከተዘገበ በኋላ በኤአይ የተሰሩ ይዘቶቿን ከኢንስታግራም እና ቲክቶክ ገጿ ላይ አጥፍታዋለች።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ለ10 ሚሊዮን የቲክቶክ እና 50 ሺህ የኢንስታግራም ተከታዮቿ ምሥሎቹን እንዴት መሥራት እንደሚቻል የሚያስገነዝብ ትምህርትን ጨምሮ በኤአይ የተሰሩ ይዘቶችን አጋርታለች።
የራሷ የቤተሰብ ታሪክም የሚገኝበት ሲሆን ሌሎች ተመልካቾችም የሚወዷቸው የሞቱ ሰዎች ምሥል እንዲሰራላቸው ጠይቀዋል።
ይህን አገልግሎት ለማግኘት የሚጠበቅባቸው የሟች ወዳጃቸውን እና የእነርሱን ፎቶ መስጠት ነው። ከዚያም ኤአይ በሚጠይቁት ጥያቄ መሠረት ምሥሉን አቀናብሮ ይሰራዋል።
የካሜንስክ ኡራልስኪይ ነዋሪዋ አና ኮራብሌቫ ከእህቷ ጋር በመሆን በኤአይ የተሰሩ ቪዲዮዎችን መሥራት የጀመረችው ካለፈው ዓመት ጀምሮ ነው።
"የስንብት ቪዲዮ" ፕሮጀክቷ ዓላማ ያልተቋጨ ስንብት ውስጥ ያሉ ሰዎችን መርዳት እና ባሎቻቸውን፣ ወላጆቻቸውን እና ልጆቻቸውን" እንዲቀበሉ እድል መስጠት ነው።
"መጀመሪያ ላይ እነዚህን ቪዲዮዎች መሥራት ስጀምር በየቀኑ አለቅስ ነበር። በጊዜ ሒደት ግን ስሜቴን ከሥራዬ መለየት እንዳለብኝ ተማርኩ" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
ኮራብሌቫ እንደምትለው ብዙ ጥያቄዎች የሚቀርቡላት ሩሲያ ከአራት ዓመት በፊት በዩክሬን ላይ ሙሉ ወረራ ከፈፀመችት ጊዜ አንስቶ በጦር ግንባር ከተገደሉ ወታደሮች ቤተሰቦች ነው።
የሩሲያ መንግሥት በጦርነቱ የሞቱ ወታደሮችን ትክክለና ቁጥር ባይገልጽም ቢቢሲ ከሩሲያው የዜና ወኪል ሜዲያዞና እና በጎ ፈቃደኞች ቡድን ጋር በመሆን የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 225 ሺህ እንደሚሆን አረጋግጧል።
የሟቾች ቁጥር ከዚህም እንደሚበልጥ ይታመናል።
በሌሎች በኦንላየን በሚዘዋወሩ የኤአይ ቪዲዮዎች ደግሞ አሁንም በሕይወት ያሉ የሩሲያ ወታደሮችን አሳይተዋል። በአንዳንዶቹ ምሥሎችም ሴቶች በእጃቸው ላይ የመላዕክት ክንፎች አድርገው ከጉዳት ሲሸፍኗቸው አሳይተዋል።
የሩሲያ ወታደሮች እንደ ጥቃት ተከላካይ እና መላዕክት ተደርገው የተሳሉበት እነዚህ ቪዲዮዎች በዩክሬንያውያን ዘንድ ቁጣን ቀስቅሰዋል።
አንዳንድ ዩክሬናውያን "ልጆቻችንን በመግደል በደም ገንዘብ ለማግኘት የተሰማሩ፣ 'ጀግኖቻችን' የምትሏቸውን ወታደሮች በማሳየታችሁ ልታፍሩ ይገባል" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በሩሲያ ዓለም አቀፍ የኤኤይ ምሥሎችን ለመሥራት የሚያስችል መሣሪያ (ቱል) ማግኘት አስቸጋሪ ነው።
በመሆኑም በርካታ ሰዎች በራሳቸው አቅም እንዲህ ዓይነት ምሥሎችን ለመሥራት ይቸገራሉ።
በዚህም ምክንያት የኤአይ የይዘት ፈጣሪ ወደሆኑት ካትያ ጂን እና አና ኮራብሌቫ ያሉ ባለሙያዎችን ይጠይቃሉ።
በሩሲያ በኤአይ የተሰራ ወታደራዊ ፎቶ እና ቪዲዮ ለማሰራት ከ2 ፓውንድ እስከ 100 ፓውንድ ድረስ ያስወጣል።
ይህ ግን በሥራው ጥራት ላይ ይወሰናል።
የኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ተመራማሪዋ ባስኒስካ እንዲህ ያሉ ቪዲዮዎች "በሥነ ምግባር ረገድም ሆነ በሥነ ልቦና ላይ ጥልቅ ችግር የሚያስከትሉ ናቸው" ብላለች።
የኤአይ ምሥሎች ሰዎች ሃዘናቸውን እንዲወጡ ይረዱ አሊያም በተቃራኒው ሃዘናቸውን ያባብሱ እንደሆነ ግልጽ እንዳልሆነም ተመራማሪዋ ገልጸዋል።
"ሁላችንም በቴክኖሎጂ ዘመን እና በባህል ለውጥ ሙከራ ውስጥ ነው ያለነው" ብለዋል።
የሞቱ የሚወዷቸው ሰዎች ምሥልን በኤአይ ያሰሩ የተወሰኑ ሰዎች ሃዘናቸውን ለማቃለል በተወሰነ መልኩ እንደጠቀማቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አንዲት ሴት በበኩላቸው " ልጄን በድጋሜ ላቅፈው እንደማልችል ቴክኖሎጂ ረድቶኛል? አልረዳኝም! ይህ ቅዠት ነው" ብለዋል።
ሐውልቱን ለማሰራት በኤአይ የተሰራ የቀድሞ ባለቤቷን ምሥል የገዛች ሴትም በመኝታ ቤቷ ግድግዳ ላይ ሌሎች ሁለት ምሥሎቹን እንደሰቀለች ተናግራለች።
ሌሎችም ቪዲዮዎቹ ከእነዚያ ከምንወዳቸው ሰዎች ጋር ግንኙነት እንዳለን እንዲሰማን ያደርጋሉ ብለዋል።
አንዲት ሩሲያዊት ሴትም "ከምወደው ሰው ጋር እንዲሆን ኤአይ ይህንን ዕድል ስለሰለጠኸኝ አመሰግናለሁ፤ ከተለየኸኝ በቅርቡ ሁለት ዓመት ይሞላል" ስትል በባለቤቷ የስንብት ቪዲዮ ላይ ጽፋለች።