ዩክሬን በሩሲያ ተፈፅመዋል የተባሉ 21 ሺህ የጦር ወንጀሎችን እየመረመርኩ ነው አለች

ታትሟል

ሩሲያ በዩክሬን ወረራ ከፈጸመችበት ጊዜ አንስቶ ጦሯ ፈፅሟቸዋል የተባሉ ከ21 ሺህ በላይ የጦር ወንጀሎችን እየመረመረች እንደሆነ ዩክሬን አስታወቀች።

የዩክሬን ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ኢሪና ቬኔዲክቶቫ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በቀን ከ200 እስከ 300 የሚደርሱ የጦር ወንጀሎች ሪፖርት እየደረሳቸው ነው።

በርካታ የፍርድ ሂደቶች የሩሲያ ጦር በሌሉበት እንደሚካሄድ ተናግረው፤ ነገር ግን ክሱን የመቀጠል ጉዳይ "የፍትህ ጥያቄ" መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።

ሩሲያ በያዝነው ዓመት የካቲት አጋማሽ ላይ በዩክሬን ወረራ የፈጸመች ሲሆን ፈፅማዋለች የሚባሉ የጦር ወንጀል ክሶችንም ውድቅ አድርጋለች።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ከቢቢሲ ዎርልድ አውት ሶርስ ከተሰኘው ፕሮግራም ጋር ባደረጉት ቆይታ ሲቪሎችን የገደሉ፣ ያሰቃዩ ወይም የደፈሩ የሩሲያ ወታደሮች “ሁሉም ፍርድ ቤት ይቀርባሉ፤ ይህ የጊዜ ጉዳይ ብቻ መሆኑን ሊረዱ ይገባል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ምንም እንኳን የተቋቋመው ቡድን መላው ዩክሬንን ባካለለ መልኩ እየሰራ ቢሆንም አንዳንድ ሰዎች እና አካባቢዎች ላይ ተደራሽነት ባለመኖሩ የተባሉ የጦር ወንጀሎችን “በትክክል እና በብቃት” መመርመር አለመቻሉን ተናግረዋል።

ይህም በሩሲያ ጦር የተያዙ የዩክሬን ግዛቶችን በተመለከተ ነው።

ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ እንዳስረዱት በግንቦት ወር ወደ 600 የሚጠጉ ተጠርጣሪዎች ተለይተው 80 ክሶች መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በዩክሬን ለፍርድ የቀረበው የመጀመሪያው የሩሲያ ወታደር ቫዲም ሺሺማሪን፣ አንድ ሰላማዊ ሰው በመግደል ወንጀል በግንቦት ወር የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል።

ዩክሬን፣ የሩሲያ ወታደሮች አጠር ላለ ጊዜ ተቆጣጥረዋቸው በነበሩ በቡቻ፣ ቦሮዲያንካ እና በዋና ከተማዋ ኪዬቭ አቅራቢያ ባሉ ግዛቶች በርካታ የጅምላ መቃብሮችን ማግኘቷን አስታውቃለች።

የዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በበኩሉ ዩክሬንን “የወንጀል ትዕይንት” ሲል የገለጻት ሲሆን ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የመርማሪ ቡድን ወደ አገሪቱ በመላክ በርካታ ምርመራዎች ላይ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።

ሩስያ ጦሯ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ አድርጓል የሚባለውን ተደጋጋሚ ክስ ውድቅ አድርገዋለች።