ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ጆንሰን ድጋፍ ቢያጡም በሥልጣን ለመቆየት እየታገሉ ነው
የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቻቸው አስተዳደሩን በመቃወም ከኃላፊነታቸው ቢለቁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን ለመቆየት እየታገሉ ነው።
የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፕሪቲ ፓቴል እና የትራንስፖርት ፀሐፊው ግራንት ሻፕስን ጨምሮ በርካታ ታማኝ ደጋፊዎቻቸው በትናንትናው ዕለት ከሥልጣን እንዲወርዱ ቢጠይቁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በእምቢተኝነታቸው ጸንተዋል።
የዌልሽ ጸሐፊው ሲሞን ሃርት ከኃላፊነታቸው የለቀቁ የመጨረሻው የካቢኔ ሚኒስትር ሲሆኑ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሱኤላ ብራቨርማን በበኩላቸው በአመራሩ ላይ ጥያቄ እያነሱ ነው።
ነገር ግን ቦሪስ ጆንሰን በሥልጣን ለመቀጠል ከመራጮቻቸው የተሰጣቸው ኃላፊነት እንዳለ አጥብቀው እየተናገሩ ነው።
ተቺዎቻቸው ላይ ባነጣጠረ መልኩም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስደንጋጭ የተባለ እርምጃን ወስደዋል የተባለ ሲሆን በዚህም “ሌቭሊንግ አፕ” የተባለው የመንግሥት ፖሊሲ ጸሐፊ የሆኑትን ሚካኤል ጎቭን አሰናብተዋል።
ጸሐፊውን የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት፣ዳውኒንግ ስትሪት ምንጭ “እባብ” በማለት የጠራቸው ሲሆን “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲሰናበቱ ጥሪ አደርጋለሁ በማለት ለሚዲያዎች በደስታ በተደጋጋሚ ሲናገርም ተሰምቷል” ብሏል።
በብሬግዚት ዘመቻ ወቅት አጋር የነበሩት ሚካኤል ጎቭ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቶሪ አመራርን እንዳይጨብጡ እንዲሁም ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ማሳሳበቸው ተነግሯል።
ጸሐፊው የተባረሩት ረቡዕ ማምሻውን ሲሆን ይህም ክብረ ወሰን በሚባል ሁኔታ ከ40 በላይ ሚኒስትሮች እና ረዳቶቻቸው ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ነው።
ትናንት አመሻሹ ላይም ቢሆን ከኃላፊነታቸው የሚለቁ ባለሥልጣናት የቀጠለ ሲሆን የዌልሱ ጸሐፊ ሃርት ከምሽቱ አምስት ሰዓት በፊት የለቀቁ የመጨረሻ ባለሥልጣን ናቸው።
ሃርት መልቀቃቸውን አስመልክቶ “ሌላ አማራጭ የለም “ ብለዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ባልደረቦች በግል እና በአደባባይ “ሁኔታዎችን እንዲያስተካክሉ እርዳታ አድርገውላቸው ነበር። ነገር ግን ይህ የሚቻልበት ደረጃን እንዳለፍን የሚሰማኝ በሃዘን ነው” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሥልጣን እንዲነሱ ለማሳመን ከሞከሩ የካቢኔ አባላት ቡድን ውስጥ አንዱ ነበሩ ጸሐፊው። ከሳቸውም በተጨማሪ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ፓቴል፣ የትራንስፖርት ፀሀፊ ሻፕስ እና የቢዝነስ ጸሐፊ ክዋሲ ኳርትንግ ይገኙበታል።
በሥልጣናቸው ላይ ከፍተኛ ችግር የተጋረጠባቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ባለሥልጣኖቻቸው በመልቀቃቸው 20 ሚኒስትሮችንም እንደ አዲስ መተካት አለባቸው።