የትራምፕ ቡድን የውስጥ መረጃዬ በኢራን ተጠልፎብኛል አለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የዶናልድ ትራምፕ ምርጫ ቅስቀሳ ቡድን የውስጥ የመረጃ ቅብብሎሼ በኢራን የመረጃ ሞጭላፊዎች የጠለፋ ሙከራ ሳይደረግበት አልቀረም አለ።
ፖለቲኮ የተሰኘው የአሜሪካ የዜና ድረገጽ በበኩሉ የትራምፕ ቡድን ያቀረበውን አቤቡታ ዐይነት ተከታታይ ኢሜሎች ምናልባትም ከዚሁ ጠላፊ ቡድን ሲደርሱት እንደነበር ይፋ አድርጓል።
ፖለቲኮ ይደርሱት የነበሩት ኤሌክትሮኒክ ደብዳቤዎች በተለይ ስለ ኦሃዮ የሕዝብ እንደራሴ ጄዲ ቫንስ ዝርዝር መረጃ የያዙ ናቸው።
ቫንስ የትራምፕ ምክትል ሆነው ለምርጫ እየተወዳደሩ እንደሆነ ይታወቃል።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ግብረ ኃይል በበኩሉ መረጃዎቹ አሜሪካንን አምርረው ከሚጠሉ የውጭ ኃይሎች የሚላኩ ነበሩ ሲል ጣቱን ወደ ኢራን ጠቁሟል።
ፖለቲኮ በበኩሉ የመረጃዎቹን እውነተኝነት አረጋግጫለሁ ያለ ሲሆን ቢቢሲ በግሉ ይህን አላረጋገጠም።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ግብረ ኃይል መረጃ ስርሰራ በኢራን ተፈጽሞብኛል ይበል እንጂ ይህን የሚያረጋግጥ አንድም ማስረጃ አላቀረበም።
ይህ በኢራን ላይ የቀረበው ክስ ማይክሮሶፍት ተመሳሳይ ክስ ባቀረበ በነገታው የቀረበ መሆኑ ነው።
ማይክሮሶፍት ባወጣው አንድ ጥናት በሰኔ ወር በአንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ እጩ ላይ ከኢራን የመረጃ ምንተፋ ሙከራ መደረጉን ያሳያል። ሆኖም አጩው ማን እንደሆነ በስም አልገለጸም።
ማይክሮሶፍት እንደሚለው ባለፉት ወራት ጤናማ የሚመስሉና መረጃን ለመመንተፍ ያለሙ የኤሌክትሮኒክ ኢሜሎች ከኢራን በኩል ሲላኩ ነበር።
የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ግብረ ኃይል ስቴቨን ቸንግ የማይክሮሶፍት መረጃ በሰኔ ወር በሴናተር ቫንስ ላይ ከተደረገው የጠለፋ ሙከራ ጋር የሚገጥም ነው ብለዋል።
“ትራምፕ ወደ ሥልጣን ከመጡ ኢራን የሽብር ተግባሯን መቀጠል እንደማትችል ታውቃለች። ለዚህ ነው ኢላማ ያደረጉን” ብለዋል ኃላፊው።
ፖለቲኮ የዜና ድረ ገጽ እንደሚለው ከባለፈው ሐምሌ ወዲህ ራሱን ሮበርት ብሎ ከሚጠራ ሰው ተከታታይ የኤሌክትሮኒክ ደብዳቤዎች ይደርሱት እንደነበረና 271 ገጽ የሚሆን ዶሴ፣ ይዘቱ በዋናነት በትራምፕ ምክትል ሴናተር ቫንስ ፖለቲካዊ ሕይወት ዙርያ የሚያጠነጥን እንደነር ይፋ አድርጓል።
ሌላው ከጠላፊዎች ተላከ የተባለው መረጃ ደግሞ በፍሎሪዳው ሴናተር ማርኮ ሩቢዮ ዙርያ የሚያተኩር ነው ብሏል።
ማይክሮሶፍት እንደሚለው ኢራን የምትደግፋቸው የመረጃ ሰርሳሪዎች ባለፉት ሦስት የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫዎች እጃቸውን ሳያስገቡ አልቀረም።
የአሜሪካ የመረጃ ምንጮች ኢራን ትራምፕን ለማስገደል ፍላጎት እንዳላት የሚጠቁሙ ናቸው።
ከሳምንታት በፊት በፔኒሲልቬኒያ ዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ መደረጉ አይዘነጋም። ሆኖም ይህ ሙከራ በኢራን የተደገፈ ስለመሆኑ ምንም መረጃ አልተገኘም።
ባለፈው ማክሰኞ ደግሞ የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ አንድ ፓኪስታናዊን 'የአሜሪካ ባለሥልጣናትን ለመግደል ከኢራን ጋር ግንኙነት አድርገሃል' በሚል ክስ መስርተውበታል።
በነዚህ ክሶች ዙርያ የኢራን መንግሥት አስተያየት ለማካተት ቢቢሲ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።












