ዩክሬን እና ሩሲያ ከፍተኛ የተባለ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃቶችን ተሰነዛዘሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 3 ደቂቃ

የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሁለቱም አገራት ግዙፍ የተባለውን የሰው አልባ አውሮፕላኖች (ድሮን) ጥቃት ፈጸሙ።

የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር በስድስት ክልሎች 84 የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች ማክሸፉን ገልጿል። አንዳንዶቹ ሞስኮ ዒላማ ያደረጉ እንደነበር ተገልጿል። በዚህም ምክንያት ከዋና ከተማዋ ዋና ዋና ሦስት አውሮፕላን ማረፊያዎች የሚነሱ እና የሚያርፉ በረራዎች እንዲቀየሩ ተገደዋል።

የዩክሬን አየር ኃይል በበኩሉ ሩሲያ ቅዳሜ ምሽት 145 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ወደ ሁሉም የአገሪቱ ክፍል መላኳን እና አብዛኞቹ መመታታቸውን አስታውቋል።

ተመራጩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግጭቱን ለማስቆም በሁለቱም ወገኖች ላይ ጫና ሊያደርጉ ይችላሉ ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው ይህ ጥቃት የተሰነዝረው።

ዩክሬን በሞስኮ ላይ ያደረገችው የጥቃት ሙከራ ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመዲናይቱ ላይ ያደረሰችው ትልቁ ጥቃት ነው። የክልሉ አስተዳዳሪም “ግዙፍ” ነው ሲሉም ገልጸውታል።

አብዛኞቹ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በራመንስኮዬ፣ ኮሎምና እና ዶሞዴዶቮ አውራጃዎች መመታታቸውን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።

ከሞስኮ ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ በምትገኘው ራመንስኮዬ በድሮኖቹ ስብርባሪ ምክንያት አምስት ሰዎች ቆስለዋል እንዲሁም አራት ቤቶች በእሳት መያያዛቸውን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል። በከተማዋ ብቻ 34 ሰው አልባ አውሮፕላኖች መመታታቸውን አክሎ ገልጿል።

መስከረም ወር ላይ በራሜንስኮይ በደረሰ የድሮን ጥቃት አንዲት ሴት ተገድላለች። ባለፈው ዓመት በግንቦት ወር በማዕከላዊ ሞስኮ በሚገኘው ክሬምሊን አቅራቢያ ሁለት ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንዲወድሙ ሲደረግ በማዕከላዊ ሞስኮ ደግሞ በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ወድመዋል።

በዩክሬን ደግሞ በኦዴሳ በደረሰ የሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ቢያንስ ሁለት ሰዎች ቆስለዋል። ከጥቃቱ በኋላ የወጡ ምሥሎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ከአንዳንድ ሕንጻዎች በእሳት ተያይዘው ታይተዋል።

የዩክሬን አየር ኃይል እንዳስታወቀው ደግሞ 62 ኢራን ሠራሽ የሩሲያ ድሮኖች ሲመቱ 67ቱ “ከሽፈዋል” ተብሏል። ተጨማሪ 10 ድሮኖች ደግሞ ከዩክሬንን አየር ክልል ወጥተው ወደ ሩሲያ እና ወደ ጎረቤት አገር ቤላሩስ እና ሞልዶቫ በማምራት ላይ መሆናቸውን አክሎ ገልጿል።

የሩሲያ ወታደሮች ከአውሮፓውያኑ መጋቢት 2022 ወዲህ በጥቅምት ወር ትልቁን አካባቢን መቆጣጠር መቻላቸው በተነገረበት ወቅት ነው ይህ የሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት የተፈጸመው ሲል ኢንስቲትዩት ኦፍ ዋር ዳታን ጠቅሶ ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ዋና አዛዥ ሰር ቶኒ ራዳኪን ለቢቢሲ ሰንዴይ እንደገለጹት ከሆነ ሩሲያ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ በርካታ ሠራዊት ያጣችበት ወር መሆኑን ጠቁመዋል።

የሩሲያ ወታደሮች በጥቅምት ወር ብቻ በአማካይ ወደ አንድ ሺህ 500 የሚጠጉ ወታደሮችን “በየቀኑ” በሞት እና በጉዳት ያጣሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ትራምፕ በዩናይትድ ስቴትስ በምርጫ ካሸነፉበት ወዲህ የሁለቱን አገራት ግጭት እንዴት እንደያስቆሙ ግምቶች እየተሰጡ ነው።

ተመራጩ ፕሬዝዳንት በምርጫ ቅስቀሳቸው ላይ ጦርነቱን “በአንድ ቀን” ማስቆም እንደሚችሉ ደጋግመው ቢናገሩም እንዴት እንደሚያደርጉት ግን ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

የትራምፕ አማካሪ የነበሩት ብራያን ላንዛ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ከሆነ አዲሱ አስተዳደር ዩክሬን ግዛቶቿን ከሩሲያ እንድታስመልስ ከማስቻል ይልቅ ሰላምን በማስፈን ላይ ያተኩራል።

የትራምፕ ቃል አቀባይ ግን ላንዛ “ለትራምፕ አይናገሩም” በማለት ተመራጩን ፕሬዝዳንት ከጉዳዩ አርቀዋል።

የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ እሑድ ዕለት በመንግሥታዊ መገናኛ ብዙኃን በኩል ከመጪው የአሜሪካ አስተዳደር “አዎንታዊ” ምልክቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ሰላምን ስለማስፈን እንጂ ሩሲያ እንድትሸነፍ ፍላጎት እንደሌላቸው ተናግረዋል።

ትራምፕ በምርጫ ካሸነፉ በኋላ “ለግማሽ ሰዓት ያህል” ከዩክሬኑን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪን ጋር መነጋገራቸውን ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ዜለንስኪ ቀደም ሲል ግዛታቸውን ለሩሲያ አሳልፎ መስጠትን እንደማይቀበሉት ተናግረው ያለ አሜሪካ እርዳታ ዩክሬን ጦርነቱን እንደማታሸንፍ አክለዋል።