በአመፀኛ ወሮበሎች የምትታመሰው ሄይቲ ጠቅላይ ሚኒስትር በ6 ወራቸው ከሥልጣን ተባረሩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሄይቲው ጠቅላይ ሚኒስትር ጌሪ ኮኒል በ6 ወራቸው ከሥልጣን መባረራቸውን ሀገሪቱን የሚያስተዳድረው ምክር ቤት አስታውቋል።

የምክር ቤቱ ዘጠኝ አባላት የፈረሙት ትዕዛዝ እንደሚያሳየው ከሥልጣን በተባረሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ምትክ ነጋዴው እና የቀድሞው የሄይቲ ሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል አሊክስ ዲዲዬን ሾሟል።

የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ባልደረባ የነበሩት ኮኒል ወደ ሥልጣን የመጡት ሀገሪቱን ከታጠቁ ወሮበሎች እንዲታደጉ ነበር። ሰውዬው በሄይቲ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ ሥልጣን ላይ ይቆያሉ ተብሎ ቢጠበቅም በግማሽ ዓመት ከመንበራቸው ተባረዋል።

ሄይቲ ከአውሮፓውያኑ 2016 በኋላ ምርጫ አካሂዳ አታውቅም።

ከሥልጣን መወገዳቸውን የተቃወሙት ኮኒል በፃፉት ደብዳቤ የሄይቲን የወደፊት ዕጣ ፈንታ “አደጋ ላይ የሚጥል” ነው ብለዋል ሲል ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

ሄይቲ በአሁኑ ወቅት ፕሬዝደንትም ሆነ ፓርላማ የላትም። በሀገሪቱ ሕገ-መንግሥት መሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን ማንሳት የሚችለው የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ብቻ ነው።

ኮኒል ሥልጣን የያዙት ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጨረሻ ነበር።

“ይህ ጉዳይ የትኛውንም ዓይነት ሕጋዊም ሆነ ሕገ-መንግሥታዊ መሠረት የለውም። ሕጋዊነቱ እጅግ አጠራጣሪ ነው” ይላል ኮኒል የፃፉት ደብዳቤ።

የሄይቲ የሽግግር መንግሥት ፕሬዝደንታዊ ምክር ቤት ባለፈው ሚዘያዚያ አሪዬል ሄንሪ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ነው የተቋቋመው። የቀድሞው መሪ ሄንሪ ከሥልጣን እንዲወገዱ የተደረጉት የወሮበሎች ቡድን ጥምረት የዋና ከተማዋ ፖርት አው ፕሪንስን የተወሰኑ ክፍሎች ከተቆጣጠረ በኋላ ነው።

ሄንሪ ባለፈው ዓመት የካቲት ስብሰባ ለመታደም ወደ ጉያና ባቀኑበት ወቅት ነው የወሮበሎች ቡድን ጥምረት ዋናው አየር ማረፊያ በመቆጣጠር እንዳይመለሱ ያደረጋቸው።

ይህን ተከትሎ ፕሬዝደንታዊው ምክር ቤት አመፅ በሰፈነባት የካሬቢያን ደሴቷ ሀገር ዲሞክራሲን እንዲያሰፍን ሥልጣን ተሰጠው።

ካለፈው ጥር ጀምሮ በወሮበሎች አመፅ ምክንያት 3600 ሰዎች ሲገደሉ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑት ደግሞ መኖሪያቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል ይላል የተባበሩት መንግሥታት ዘገባ።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው በታጠቁ ወሮበሎች እየታመሰች ያለችው ሄይቲ በዓለማችን እጅግ ደሀ ከሚባሉ ሀገራት መካከል ናት።

የመንግሥታቱ ድርጅቱ መረጃ እንደሚያሳየው ሁለት ሚሊዮን የሄይቲ ዜጎች አስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ከሀገሪቱ ሕዝብ ግማሽ ያክሉ “በቂ ምግብ የለውም።”

እጅግ አመፀኛ ከሚባሉት የወሮበላ ቡድን መሪዎች አንዱ የሆነው ጂሚ ሼሪዚዬር አሊያም በቅፅል ስሙ ባርቢኪው የታጠቁ ቡድኖች አዲስ መንግሥት በመመሥረት ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ ከሆነ አመፁን ለማስቆም ዝግጁ ነኝ ማለቱ ይታወሳል።

በሄይቲ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ የተካሄደው ከ8 ዓመታት በፊት ነው። በወቅቱ ጆቬኔል ሞይዝ የሀገሪቱ መሪ ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።

ነገር ግን በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 2021 ሞይዝ ከተገደሉ በኋላ በሀገሪቱ ፕሬዝደንት ተሹሞ አያውቅም።

በሀገሪቱ ያለው የሥልጣን ሽኩቻ የጠቀማቸው የታጠቁ ቡድኖች ግዛታቸውን በማስፋት ላይ የሚገኙ ሲሆን አብዛኛው የሀገሪቱ ክፍል ሰላም እና ፀጥታ ከራቀው ሰንበትበት ብሏል።

በአሜሪካ የሚደገፈው የኬንያ ፖሊስ ኃይል ወደ ሄይቲ አቅንቶ የሰላም ማስከበር ሥር የጀመረ ሲሆን ተጨማሪ ፖሊሶች ወደ ደሴቷ ያቀናሉ ተብሎ ይጠበቃል።