ሶማሊላንድ ሕገ ወጥ ስደተኞች እንዲወጡ ቀነ ገደብ አስቀመጠች፣ ኢትዮጵያውያን ሰግተዋል  

ታትሟል

ዓለም አቀፍ እውቅና የሌላት እና ከሶማሊያ ተነጥላ የወጣችው ሶማሊላንድ ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው የውጭ ዜጎች አገሪቱን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ አሳሰበች።

የአገሪቱ የኢሚግሬሽን አገልግሎት ሐምሌ 21/2014 ዓ.ም. ባወጣው ማሳሰቢያ እስከ መጪው ነሐሴ 11/2014 ዓ.ም. ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ለቀው እንዲወጡ ያሳስባል።

በተጨማሪም ሕገ ወጥ ስደተኞችን በሚያሰሩ ዜጎች ላይም እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል።

ከሌሎች አገራት ዜጎች በተለየ በርካታ ኢትዮጵያውያን በሶማሊላንድ ውስጥ በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ በመሆናቸው ይህ ውሳኔ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል።

በሶማሊላንድ የኢትዮጵያ ወኪል የሆኑት አቶ ሰኢድ መሐመድ ጂብሪል ጉዳዩን ቆንስላ ጽህፈት ቤታቸው እየተከታተለው እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ከሶማሊላንድ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው። በመጪው ሦስት ቀናት ውስጥ ለውጥ ይኖራል ብለን እንገምታለን። እስካሁን ድረስ ግን በቁጥጥር ስር የዋለ ኢትዮጵያዊ የለም” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ በቀጥታ እውቅና ባትሰጥም ተጎራባች ግዛት በመሆኗ ግንኙነት ካላቸው ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ናት። የሶማሊላንድ አምባሳደር በአዲስ አበባ እንዲሁም ኢትዮጵያም በሃርጌሳ ቆንስላ ጽህፈት ቤት አላቸው።

ይህንን ተከትሎም ኢትዮጵያ የሶማሊላንድ የቅርብ አጋሮች ዝርዝር ውስጥ ትገኛለች። ኢትዮጵያ ከዓመታት በፊት ከዱባዩ ዲፒ ወርልድ ጋር የበርበራ ወደብን ለማልማት የሚያስችላትን 19 በመቶ ድርሻ መውሰዷ ብሎም ስምምነቱን የሶማሊላንድ ፓርላማ እንዳጸደቀው ይታወሳል።

ይህ ስምምነት በያዝነው ዓመት ኢትዮጵያ ያላት ድርሻ መቋረጡን የሚያሳዩ መረጃዎች ከሶማሊላንድ መንግሥት ዘንድ የወጡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ሂደቱን አስተባብሏል። ጉዳዩም ገና መቋጫ ያልተበጀለት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ገልጾ ነበር።

መቀመጫቸውን በሶማሊላንድ ያደረጉት እና ከሚሰሩበት ተቋም ፖሊሲ ጋር ተያይዞ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈቀዱት ተንታኝ እንደሚሉት፣ ይህ አዲስ እርምጃ እንዳልሆነ እና ከአራት ዓመት በፊት ተመሳሳይ ውሳኔ ተላልፎ እንደነበር ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አክለውም ይህ የሶማሊላንድ ውሳኔ ከጫት ንግድ እና ከሌሎች የደኅንነት እንዲሁም የፀጥታ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ነው ብለው እንደሚያምኑ ይናገራሉ።

“በሶማሊላንድ ያሉ ስደተኞች” ሲል የኢሚግሬሽን መሥሪያ ቤቱ በድፍን ይናገር እንጂ ኢትዮጵያውያንን ኢላማ ያደረገ ነው በማለት፣ ለዚህም በአገሪቱ ከኢትዮጵያውያን ውጪ ያሉ የሌሎች አገራት ስደተኞች ጥብቅ የሰነድ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው ጠቅሰዋል።

“ለምሳሌ ፓኪስታኖች አሉ። ነገር ግን ቪዛቸው ጊዜው ካለፈ ራሱ ይቀጣሉ” ሲሉ ያክላሉ። “በሶማሊላንድ ያሉ ኢትዮጵያዊውን እንደ መደራደሪያ ናቸው። በሁለቱ መንግሥታት መካከል የጫት ንግድን የተመለከቱ ያለመግባባቶች አሉ። ከዛም ባሻገር በቅርቡ የተፈረመው የደኅንነት ስምምነት ለችግሩ ምክንያት ነው ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ በበርበራ ወደብ ልማት ላይ የወሰደችው ድርሻ መሰረዙ ከተሰማ ወዲህ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን የያዘ ልዑክ ወደ ሃርጌሳ ተልኮ ነበር።

የትራንስፖርት ሚንስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ እንዲሁም የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን ልዑኩን በሐምሌ ወር መጀመሪያ መርተው ተጉዘውም ነበር።

በዚህ ሳምንት አጋማሽም በአገር መከላከያ የደኅንነት ሹም የተመራ ልዑክ ሃርጌሳ መግባቱን የሶማሊያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ታዲያ እነዚህ የንግድ ጉዳዮች እንዳሉ ሆነው ሁለቱ አገራት በቅርቡ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን በሃርጌሳ መቀመጫቸውን ያደረጉት የሰላም እና የደኅንነት ተንታኝ የሆኑት ግለሰብ ይናገራሉ።

የሶማሊላንድ እና የኢትዮጵያ ድንበር በቀጭን ገመድ የሚለይ እና ሰፊ የንግድ እና ማኅበራዊ ልውውጦች ያሉበት ነው። እንዲሁም ኢትዮጵያውያን ያለጥብቅ የድንበር ቁጥጥር ሶማሊላንድ ገብተው ይወጣሉ፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉትም በተለያዩ ሥራዎች ላይ ተሰማርተው ይኖራሉ።

በተለይም የቤት ውስጥ ሥራ፣ ፀጉር ቤቶች እንዲሁም አነስተኛ ምግብ ቤቶችን ከፍተው ይሰራሉ። በቶግ ወቻሌ ከተማም በርካታ የኢትዮጵያ ባንኮች ቅርጫፎቻቸውን ከፍተው ይሰራሉ።

በኢትዮጵያ እና በሶማሊላንድ አዋሳኝ አካባቢዎችና ድንበር ተሻግሮ ባሉ ስፍራዎች ከፍተኛ የንግድ እንቅስቃሴ የሚደረግ ሲሆን፣ በሁለቱም በኩል ተንካራ የሆነ ግንኙነት እንዳለ ይታመናል።

የሶማሊያ ታጣቂ ቡድን አል ሻባብ ከሳምንት በፊት ወደ ኢትዮጵያ ዘልቆ በመግባት ጥቃት ከፈጸመ በኋላ የኢትዮጵያ ሠራዊት እና የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል በቡድኑ ታጣቂዎች ላይ እርምጃ መውሰዳቸውና ከፍተኛ አመራሮቹ መገደላቸው መነገሩ ይታወሳል።

ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ ድንበር በኩል አስካሁን ይህ ነው የሚባል የፀጥታ ስጋት ያልገጠማት ሲሆን፣ ይህንንም ለማጠናከር የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ባለፉት ቀናት በሃርጌሳ ጉብኝት ማድረጋቸው ተዘግቧል።