ሜዳ ላይ ወድቀው የሚሞቱ ተጫዋቾች ቁጥር በመጨመሩ የጤና ክትትል እንዲደረግ ድሮግባ ጠየቀ

ዲደዬር ድሮግባ
ታትሟል

እውቁ የቀድሞ እግር ኳስ ተጫዋች ዲዲዬር ድሮግባ በአገሩ አይቮሪ ኮስት አንድ ተጫዋች በጨዋታ ወቅት ሜዳ ላይ ተዝለፍልፎ ወድቆ ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ለእግር ኳስ ተጫዋቾች የተሻለ የጤና ክትትል እንዲደረግ ጠየቀ።

ሞስታፓ ሲይላ የተባለው የ21 ዓመቱ ተጫዋች እሑድ ዕለት ለክለቡ ሬሲንግ ክለብ አቢጃን በአገሪቱ ትልቁ በሆነው ሊግ እየተጫወተ ሳለ ተዝለፍልፎ ወድቆ ወደ ሆስፒታል እየተወሰደ ሳለ ሕይወቱ ማለፉን ክለቡ አስታውቋል።

የቼልሲ እና የአይቮሪ ኮስት የፊት መስመር ተጫዋች የነበረው ድሮግባ የአገሩ ተጫዋቾች በእግር ኳስ ተቋማት አማካይነት ተጨማሪ የጤና ክትትል ሊደረግላቸው ይገባል ብሏል።

“ከአራት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በፕሮፌሽናል ሊግ የሚጫወቱ ሦስት አይቮሪያውያን ሕይወታቸው አልፏል። ለፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጫዋቾች የሚደረገው አስገዳጁ የጤና ምርመራ የታለ? የደም ምርመራው፣ ኢኬጂ፣ የአእምሮ ጤና ክትትል የታለ? የስፖርት ጤና የሚመጣው መቼ ነው” ሲል ድሮግባ ጠይቋል።

የሬሲንግ ክለብ አቢጃን ክለብ ፕሬዝዳንት ሎጎሲን ሲሴ “ትልቅ ተስፋ የነበረው ኮከብ በጊዜ አሸለበ” ሲሉ ተጫዋቹን የገለጹት ሲሆን፤ የአገሪቱ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም በሞስታፓ ሲይላ ሞት የተሰማውን ሐዘን ገልጿል።

ሲይላ የተባለው ተጫዋች ሬሲንግ ክለብ አቢጃን ክለብ ከመቀላቀሉ በፊት ከቀድሞ ክለቡ ዲጆሊባ ኤሲ ጋር የ2022 ማሊያን አሸናፊ ሆኖ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙ እግር ኳስ አፍቃሪዎች በልምምድ ያለ ተጫዋች ሕይወቱ ካለፈ በኋላ ሐዘናቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

የሪቻርድ ቤይ እግር ኳስ ክለብ ተከላካይ የነበረው ሲፓማንላ ሞቶሎ ትናንት ማክሰኞ ልምምድ ላይ ሳለ እራሱን ስቶ ከወደቀ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

በአገሪቱ ፕሪሚየር ሊግ የሚሳተፈው ክለብ የተጫዋቹን ሞት በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ወደፊት አጋራለሁ ብሏል።