የሩሜኒያ ፖሊስ ከአንድሩ ቴት መኖሪያ ቤት ቅንጡ መኪኖችን ያዘ

ፖሊስ ከያዛቸው ከአንድሩ ቴት ቅንጡ መኪኖች አንዷ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፖሊስ ከያዛቸው ከአንድሩ ቴት ቅንጡ መኪኖች አንዷ
ታትሟል

የሩሜንያ ፖሊስ ከብሪታኒያዊ-አሜሪካዊው የማኅበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ አንድሩ ቴት መኖሪያ ቤት በርካታ ቅንጡ መኪኖችን ያዘ።

ከሳምንታት በፊት የአገሪቱ ፖሊስ አንድሩ ቴትን ከወንድሙ ትረስቲያን ጋር በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ከአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር አውሏቸው እንደነበረ ይታወሳል።

በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት ወንድማማቾች ክሱን እንደማይቀበሉት በጠበቃቸው በኩል አስታውቀዋል።

የሩሜኒያ ፖሊስ ቅዳሜ ዕለት ቡካሬስት ከሚገኘው የቴት የግል ንብረት ከሆነ ቦታ ሮልስ-ሮይስ፣ ቢኤምደብሊው እና መርሴዲስ-ቤንዝን ጨምሮ በርካታ ቅንጡ መኪኖችን መያዙን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

የቴት ጠበቃ እስካሁን በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር የለም።

በዚህ ሳምንት መጨረሻ ላይ ቴት ከእስር ወጥቶ ጉዳዩን ለመከታተል ያቀረበው አቤቱታ ውድቅ ተደርጎበታል። ጉዳዩን እየተመለከቱ ያሉት ዳኛ በእስር ሆኖ መቆየት አለበት ብለዋል።

ቴት ቡካሬስት ወደሚገኘው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ሲያመራ ቁርዓን ሊሆን እንደሚችል የተገመተ ነገር በእጁ ይዞ ታይቷል።

ፖሊስ አንድሩ ቴትን በፈረንጆቹ 2022 ማብቂያ ላይ በቁጥጥር ሥር ካዋለው በኋላ ‘በተደራጀ የወንጀል ቡድን’ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው 6 ሴቶችን ለይቻለሁ ብሎ ነበር።

ሴቶቹ በካሜራ ፊት የወሲብ ተግባር እንዲፈጽሙ በኃይል ተገደው ነበር ብሏል ፖሊስ።

ጠበቃው ግን ደንበኞቼ የቀረቡባቸውን ክሶች ፈጽሞ አይቀበሉም ብለዋል።

ራሱን “ለሴቶች ጥልቅ ጥላቻ ያለው ሰው” አድርጎ የሚገልጸው ቴት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ በሚያጸባርቃቸው አመለካከቶች ተጽእኖ ፈጣሪነቱ ባለፉት ዓመታት እጅጉን ጨምሯል።

አንድሩ ቴት በቀደመ የስፖርት ሕይወቱ ከአንዴም አራት ግዜ የኪክቦክስ ውድድር የዓለም ሻምፒዮና ሆኗል።

አንድሪው ቴት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አሁን ላይ ታዋቂ ያደረገው ግን በስፖርት ሕይወቱ ያገኘው ስኬት ሳይሆን ሴቶችን በተመለከተ የሚሰጣቸው “አጸያፊ እና አስነዋሪ” የተባሉት አስተያየቶቹ ናቸው።

ቴት በአንድ ወቅት “ሴቶች የወንዶች ንብረት ናቸው” ብሎ ነበር። በሌላ ቪዲዮ ደግሞ “እራሷን የቻለች ሴት” ብሎ ነገር የለም ብሏል።

ቴት በተደጋጋሚ በሚሰነዝራቸው የጥላቻ እና አዋራጅ ንግግሮቹ ዩቲዩብ፣ ፌስቡክ፣ ኢንስታግራም እና ቲክቶክ አግደውታል። 

ቴት ሴቶችን ከኮምፒዩተር ፊት ለፊት አስቀምጦ በኢንተርኔት አማካይነት ወንዶችን እንዲያማልሉ በማድረግ ከወንዶች በሚቀበለው ገንዘብ ሃብት እንዳፈራ ይነገራል።