እስራኤል የደረሰባትን ጥቃት ለመበቀል በሊባኖስ የሚገኙ የሄዝቦላህ ዒላማዎችን ደበደበች

የጥቃቱ ስፍራ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

በእስራኤል ቁጥጥር ስር በሚገኘው አካባቢ እግር ኳስ ሲጫወቱ የነበሩ 12 ህጻናት እና ጎልማሶች በሮኬት ጥቃት ከተገደሉ በኋላ የእስራኤል አየር ኃይል በሊባኖስ የሄዝቦላህ ዒላማዎችን መምታቱ ተገለጸ።

እስራኤል ቅዳሜ ዕለት ለተፈጸመባት የሮኬት ጥቃት የሌባኖሱን ታጣቂ ቡድን ተጠያቂ ብታደርግም ሄዝቦላህ ግን ምንም አይነት ተሳትፎ የለኝም ሲል በጥብቅ አስተባብሏል።

እሐድ ዕለት የአገሪቱ ጦር “በሊባኖስ ግዛት ውስጥ” በሚገኙ ሰባት የሄዝቦላ ዒላማዎች ላይ የአየር ጥቃት ማድረሱን ተናግሯል። ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው ግን ግልጽ አይደለም።

በእስራኤል እና በሄዝቦላ መካከል እየጨመረ ያለው ውጥረት ሁለቱ ኃይሎች ወደ ሙሉ ጦርነት ሊያስገባ ይችላል።

የእግር ኳስ ሜዳ ላይ ቅዳሜ በተሰነዘረ ጥቃት በእስራኤል ሰሜናዊ ድንበር ላይ የጠፋው የሰው ህይወት መስከረም 26 ጦርነቱ ከጀመረ ወዲህ እጅግ አስከፊው የሕይወት መጥፋት ነው ተብሏል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ቡድኑ “ከባድ ዋጋ እንደሚከፍል” በመግለጽ በሄዝቦላ ላይ የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ቃል ገብተዋል።

ከሰዓታት በኋላ የእስራኤል አየር ኃይል "የመሳሪያ ማከማቻ እና የአሸባሪ መሠረተ ልማቶችን" ጨምሮ "የሽብር ዒላማዎችን" መምታቱን አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ባወጣው መግለጫ በሁሉም ወገኖች "ከፍተኛ ጥንቃቄ” ወሳኝ ነው። ይህ ካልሆነ ሰፊ እና "ቀጠናውን አደጋ ውስጥ ሊከት" የሚችል ግጭት ይከሰታል ብሏል።

የሄዝቦላህ ቃል አቀባይ ሞሃመድ አፊፍ ለጥቃቱ ኃላፊነቱን አልተቀበሉም። ፍንዳታው የተፈጠረው በእስራኤል የጸረ ሮኬት ስህተት ነው ሲል ታጣቂ ቡድኑ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተናገረውን ዘገባ ለማረጋገጥ ቢቢሲ እየሞከረ ነው።

ምንም እንኳን እስራኤል እና ሄዝቦላ ከመስከረም 2016 በኋላ በመደበኛነት የተኩስ ልውውጥ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ይሁን እንጂ ሁለቱም ወገኖች በደቡብ ሊባኖስ ሊቀሰቀስ ከሚችል የጦርነት እርምጃዎች ተቆጥበዋል።

በአሜሪካ ጉብኝት ላይ የነበሩት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ከተያዘላቸው ጊዜ ቀደም ብለው ወደ አገራቸው እየተመለሱ ነው።

ይህ በእስራኤል ምድር ላይ የተፈጸመው ጥቃት በርካቶችን አስቆጥቷል።

በእስራኤል የድሩዝ ማህበረሰብ መሪ የሆኑት ሼክ ሞዋፋክ ታሪፍ ቁጣ በቀላቀለ መግለጫቸው “አሰቃቂው እልቂት። ሁሉንም ቀይ መስመር አልፏል” ብለዋል።

ሮኬቱ ያጠቃው ሜዳ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው “ሁለገብ ጦርነት ከፊታችን ተደቅኗል” ብለዋል።

የእስራኤል ፕሬዝዳንት አይዛክ ሄርዞግ ደግሞ ድርጊቱን “አሰቃቂ እና አስደንጋጭ አደጋ” ሲሉ ገልጸው “እስራኤል ዜጎቿን እና ሉዓላዊነቷን በጽኑ ትጠብቃለች” ብለዋል።

የሊባኖስ መንግሥትም “በሁሉም ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችን ሁሉ ያወግዛል” ከማለት ባለፈ ሁሉም ወገኖች ጦርትነት ቀስቃሽ ከሆነ ተግባራት እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርቧል።

አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረትም ጥቃቱን አውግዘዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተወካይ ቶር ዌንስላንድ ድርጊቱን አውግዘው ሁሉም ወገኖች እንዲታቀቡ አሳስበዋል።

በኤክስ ላይ ባሰፈሩት ጽሑፍ “መካከለኛው ምስራቅ የጦርነት አፋፍ ላይ ነው። ዓለም እና አካባቢው ሌላ ግጭትን መሸከም አይችሉም" ብለዋል።