ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በማዳጋስካር 32 ሰዎችን አቃጥሎ የገደለው ቡድን እየታደነ ነው
በአፍሪካዊቷ አገር ማዳጋስካር 32 ሰዎችን በቤት ውስጥ አጉረው ያቃጣሉ ግለሰቦችን የያዘ የወንጀለኞች ቡድን ለመያዝ የመንግሥት የጦር ሄሊኮፕተሮች ተሰማሩ።
ፖሊስ እንዳስታወቀው የወንጀለኛ ቡድን አባላቱ በርካታ ሰዎችን የሳር ክዳን ወዳላቸው ቤቶች ውስጥ በኃይል እንዲገቡ ካደረጉ በኋላ እሳት ለኩሰውባቸዋል።
ከዋና ከተማዋ አንታናናሪቮ በስተሰሜን በምትገኘው አንካዞቤ ግዛት ውስጥ በተፈጸመው በዚሁ ጥቃት ሰለባ ከሆኑት መካከል ሴቶች እና ህጻናት ይገኙበታል።
የማዳጋስካር የመከላከያ ሚኒስትሩ ለጥቃቱ በአካባቢው “ዳሃሎ” እየተባሉ የሚታወቁትን የከብት ዘራፊዎች ተጠያቂ አድርገዋል።
ከጥቃቱ በኋላ አካባቢውን የጎበኙት የመከላከያ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም የፀጥታ ኃይሎች በወንበዴዎች ላይ ባደረጉት ዘመቻ ሕብረተሰቡ ለኃላፊዎች መረጃ ሰጥተዋል በሚል ኢላማ ተደርጓዋል ብለው እንደሚጠረጥሩ ተናግረዋል።
ጄኔራል ሪቻርድ ራኮቶኒሪና “ይህንን ወንጀል የፈጸሙትን እና ተባባሪዎቻቸውን አሳደን እንይዛቸዋለን’’ ሲሉ ተናግረዋል።
በአካባቢው እየተንሰራፋ የመጣውን የከብት ስርቆት ለማስቆም እየተደረገ ያለው ጥረት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እጅግ በጣም ጭካኔ የተሞላባቸውን ግጭቶችን አስከትሏል።
የጥቃቱ አዲስ ሰለባ በሆነችው መንደር የተቃጠሉት ቤቶች የሚያሳዩ ምስሎች በስፋት ተሰራጭተዋል።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ከጥቃቱ ተርፈው በሕክምና ተቋማት በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ ክትትል የሚያገኙ ሦስት ሰዎችን ጎብኝተዋል።