ሊቢያ የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሶማሊያ እና የሱዳን ዜጎች ወደ ግዛቷ እንዳይገቡ ከለከለች

ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 2 ደቂቃ

የሊቢያን ምሥራቃዊ ክፍልን የሚቆጣጠሩት ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳን እና የሶማሊያ ዜጎች ወደ አገሪቱ እንዳይገቡ የሚከለክል ዕግድ ጣሉ።

ከፊሉን የሊቢያ ግዛትን የሚቆጣጠሩት በኻሊፋ ሃፍታር የሚመሩት አስተዳዳሪዎች የአራቱን የአፍሪካ ቀንድ አገራት ዜጎች እንዳይገቡ የከለከሉት በሊቢያ የባሕር ዳርቻ በኩል በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚጓዙ ስደተኞችን ለማስቆም መሆኑ ተነግሯል።

በጦርነት የተከፋፈለችው ሊቢያ ከአፍሪካ ቀንድ በተጨማሪ ከሌሎች የአፍሪካ ክፍሎች የተሻለ ሕይወትን ፍለጋ በአደጋኛ ሁኔታ የሚጓዙ ስደተኞች ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩባት ወሳኝ አገር ናት።

በሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ሰሃራ በረሃን በአስቸጋሪ ሁኔታ አቋርጠው ወደ ሊቢያ የሚደርሱ አፍሪካውያን ስደተኞች ከባድ ስቃይ እና እንግልት ሊቢያ ውስጥ የሚያጋጥማቸው መሆኑን ይናገራሉ።

በሰዎች አዘዋዋሪዎች እና በታጣቂዎች እገታ፣ እስር፣ ድብደባ እና ሰቆቃ የሚገጥማቸው ስደተኞች ከፍተኛ ገንዘብ እየከፈሉ በአደገኛ ሁኔታ በትናንሽ ጀልባዎች ሜዲትራኒያን ባሕርን ለማቋረጥ የሞከሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት ተዳርገዋል።

ይህንንም ለመቆጣጠር በሚል ምሥራቃዊ ሊቢያን የሚቆጣጠሩ ባለሥልጣናት አሁን የኢትዮጵያ፣ የኤርትራ፣ የሱዳን እና የሶማሊያ ዜጎች "በየብስ፣ በባሕር እና በአየር ወደ ሊቢያ እንዳይገቡ" ክልከላ መጣላቸውን እንዳስታወቁ አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ውሳኔው ይፋ የሆነበት መግለጫ ጨምሮም ይህ በአፍሪካ አገራት ዜጎች ላይ የተጣለው ዕገዳ ዲፕሎማቶችን፣ የጤና እና የትምህርት ዘርፍ ሠራተኞችን የሚመለከት እንዳልሆነ ገልጿል።

የሞአመር ጋዳፊ መንግሥት መውደቅን ተከትሎ ከተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት በኋላ በምሥራቅ እና በምዕራብ የተከፈለችውን ሊቢያን የሚቆጣጠሩት ኃይሎች የራሳቸውን የበላይነት ለማስጠበቅ ከሚፎካከሩባቸው ጉዳዮች መካከል የስደተኞች ጉዳይ አንዱ ነው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ምሥራቃዊ ሊቢያን የሚቆጣጠረው ኃይል በፊልድ ማርሻል ኻሊፋ ሃፍታር የሚመራ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ምዕራባዊውን የአገሪቱን ክፍል የሚቆጣጠረው ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ኦሳማ ሃማድ መንግሥት ነው።

ከሌሎች አገራት ወደ ሊቢያ የሚገቡ ስደተኞችን በተመለከተ ባለፉት ጥቂት ወራት በሁለቱ የሊቢያ ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጥረት ነግሶ ቆይቷል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ ስደተኞችን ለመቆጣጠር በተወሰዱ የጅምላ እርምጃዎች ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች መታሰራቸውን የአምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃ ያመለክታል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መረጃ መሠረት በአሁኑ ወቅት በሊቢያ ውስጥ ከ900 ሺህ በላይ ስደተኞች የሚገኙ ሲሆን፣ ከመካከላቸውም በአገራቸው የሚካሄደውን የእርስ በርስ ጦርነት የሸሹ ሱዳናውያን ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።

ወደ ሊቢያ የሚገቡት ስደተኞች ዋነኛ ዓላማቸው ወደ አውሮፓ መሻገር ሲሆን፣ በዚህም በርካቶች ትናንሽ ጀልባዎችን በመጠቀም ሜዲትራኒያንን ለመሻገር ሙከራ ሲያደርጉ ተይዘው ወደ ሊቢያ እንዲመለሱ ተደርገዋል።

ከዚያም በኋላ ስደተኞቹ በመንግሥት ቁጥጥር ስር በሚገኙ ማቆያዎች ውስጥ የሚታሰሩ ሲሆን፣ እዚያም ጥቃት፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ድብደባ፣ መደፈር እና ስቅይት እንደሚደርስባቸው እና እነዚህም በሰብአዊነት ላይ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች ጋር የሚስተካከሉ መሆናቸውን የተባበሩት መንግሥታት መርማሪዎች አመልክተዋል።

ሊቢያ አሁን ወዳለችበት ቀውስ ውስጥ የገባችው በኔቶ ድጋፍ የሞአመር ጋዳፊ መንግሥት በአውሮፓውያኑ 2011 ከተወገደ በኋላ ነው።

አገሪቱ አሁን በምሥራቃዊ እና ምዕራባዊ ክፍል ውስጥ መቀመጫቸውን ባደረጉ ሁለት መንግሥታት የምትመራ ሲሆን በተለያዩ ጊዜያትም ግጭቶች ይካሄዱባታል።