ዜሌንስኪ ተጨማሪ የደኅንነት ቢሮ ኃላፊን ከሥራ አባረሩ

የፎቶው ባለመብት, FUTURE PUBLISHING VIA GETTY IMAGES
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ የአገሪቱን የደኅንነት አገልግሎትን (ኤስቢዩ) ምክትል ዋና ዳይሬክተርን በማሰናበት ተቋሙን 'የማፅዳት' ሥራቸውን አጠናክረዋል።
ከሥራ የተባረሩት ኃላፊ በተቋሙ ውስጥ ያሉ የሩሲያ ደጋፊዎችን ተከታትለው ማስወጣት አልቻሉም ያሉት ዜሌንስኪ፤ አሁን ደግሞ ቮሎዲሚር ሆርቤንኮን አሰናብተዋል።
በበርካታ ከተሞች ያሉ የክልል ኃላፊዎችም ከሥራ መባረራቸውን ዜሌንስኪ ተናግረዋል።
የሕዝብ እንደራሴዎችም የኤስቢዩ ዋና ኃላፊ ኢቫን ባካኖቭን እና ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ኢሪና ቬኔዲክቶቫን ለማሰናበት ድምጽ ሰጥተዋል።
የዜሌንስኪ አማካሪ ሰኞ ዕለት ኃላፊዎቹ መታገዳቸውን ቢገልጹም ፕሬዝዳንቱ ምሽት ላይ በሰጡት መግለጫ ከሥልጣናቸው መነሳታቸውን ገልጸዋል።
ማክሰኞ ዕለት ፕሬዝዳንቱ በፓርላማ ቀርበው በኃላፊዎቹ ላይ የመተማመኛ ድምጽ እንዲሰጥ ጥያቄ አቅርበዋል። ጥያቄውም በአብዛኞቹ የሕዝብ እንደራሴዎች ተቀባይነት አግኝቷል።
ዜሌንስኪ በየካቲት ወር የሩሲያን ግስጋሴ ለማስቆም አልቻሉም በማለት ባካኖቭን ለመተካት መፈለጋቸውን የሚገልጹ ሪፖርቶች ለበርካታ ሳምንታት ሲሰራጩ ቆይተዋል።
ዜሌንስኪ በግል የሾሟቸው ሁለቱም ከፍተኛ ባለሥልጣናት እስካሁን የአገር ክህደት ክስ አልቀረበባቸውም። ሆኖም ድርጅታቸው በጦርነቱ የመጀመሪያ ቀናት የሩስያን ጣልቃ ገብነት የነበረበት እና በዚህም ለወረራ ተጋልጧል ተብሏል።
ከድምጽ አሰጣጡ በኋላ ንግግር ያደረጉት የዜሌንስኪ 'ሰርቫንት ኦፍ ዘ ፒፕል' ፓርቲ መሪ የሆኑት ዴቪድ አርካሚያ፤ አዲስ መረጃ በቅርቡ መውጣቱን እና ኤስቢዩን 'ማጽዳቱ' እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
አራካሚያ "ብዙ 'ማጽዳቶች ይኖራሉ። ምክንያቱም በሚያሳዝን ሁኔታ ባለፉት ዓመታት ብዙ የሩሲያ የደኅንነት ሰዎች ወደ ኤስቢዩ ሰርገው ገብተዋል። ቀደም ሲል ያልነበራቸውንም መረጃ አግኝተዋ" ብለዋል።
ዜሌንስኪ ዕሁድ ዕለት እንደገለጹት ከ60 በላይ የቀድሞ የኤስቢዩ እና የዐቃቤ ሕግ ቢሮ ሠራተኞች አሁን በሩሲያ ቁጥጥር ስር በሚገኙ አካባቢዎች ከዩክሬን በተቃራኒ እየሠሩ ነው።
የባካኖቭ ምክትል የሆኑት ቫሲል ማልዩክ የኤስቢዩ ተጠባባቂ ኃላፊ በመሆን መሾማቸውን በፕሬዚዳንቱ ድረ-ገጽ ላይ ይፋ ተደርጓል።












