የአሁኑ የማንቸስተር ዩናይትድ ቡድን 'እጅግ ደካማ የሆነው የክለቡ ስብስብ' ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, GETTY IMAGES
ባለፉት ዓመታት በማንቸስተር ዩናይትድ እና በአርሰናል መካከል የሚደረጉ ጨዋታዎች በሊጉ አናት ላይ ለመቀጥ የሚደረግ ፍልሚያ ነበር።
አሁኑ የኤሪክ ቴን ሃግ ቡድን ሚና ግን ለዋንጫ የሚፎካከረውን ቡድን ህልም የማጨናገፍ ብቻ ሆኗል። ይህም ግን አልተሳካለትም።
ሁለቱ ቡድኖች ትላንት ኦልትራፎርድ ላይ ተገናኝተው አርሰናል 1 ለምንም ማሸነፍ ችሏል።
የቀድሞው የቀያዮቹ ሰይጣኖች አማካይ ሮቢ ሳቫጅ የቀድሞ ቡድኑ ከመድፈኞቹ ጋር አቻ ለመሆን ያደረገውን ከንቱ ድካም ከተመለከተ በኋላ “ይህ ከማንቸስተር ዩናይትድ ስብስቦች ከደካማዎቹ አንዱ ነው” ሲል ተናግሯል።
አርሰናል በኦልድትራፎርድ ሦስት ነጥብ በመሰብሰብ የደረጃ ሰንጠረዡን በበላይነት ለመያዝ ችሏል። ከማንቸስተር ሲቲ ጋር ለዋንጫ የሚያደርገውን ፍልሚያ ያረጋገጠበትን ጎል ሊያንድሮ ትሮሳርድ በመጀመሪያ አጋማሽ አስቆጥሯል።
የክለቡ የቀድሞ አምበል ሮይ ኪን ለስካይ ስፖርት “በተለይ የመጨረሻው ሰላሳ ደቂቃ ለማንቸስተር ዩናይትድ መጥፎ ነበር” ብሏል።
“ዩናይትድ ምን ያህል ጥሩ አልነበረም። አርሰናሎች ያዩትን ነገር ያመኑ አይመስለኝም” ሲል አክሏል።
"ተጫዋቾቹ ራሳቸውን ማየት አለባቸው"
ከጨዋታው በፊት አሰልጣኝ ቴን ሃግ ባለፈው ሳምንት በክሪስታል ፓላስ 4 ለምንም ሽንፈት ቀምሰው ቡድናቸው እስከመጨረሻው እንዲፋለም ጠይቀዋል።
ለኪን ግን የተደረገው ፍልሚያ አልታየውም።
"የመጨረሻውን ሰላሳ ደቂቃ ብንመለከት ማንም ማንንም አይታገልም፤ ስህተት ሲሠሩ እና ሲወድቁ፤ ሁሉም ከመሮጥ ይልቅ ይራመዱ፤ አንዳቸውም ለሌላቸው ሲታገሉ አልታየም" ብሏል።
"ይህ የዩናይትድ ቡድን በጣም መጥፎ ነበር።"
በሌላ በኩል ከተመለከትነው ደግሞ ከመድፈኞቹ በ29 ነጥብ ዝቅ ብሎ፤ በስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ ለዋንጫ ከሚፋለመው ቡድን ጋር በጠባብ ውጤት መሸነፍ መጥፎ የሚባል አይደለም።
ይህ ግን በዘንድሮው የሊጉ የውድድር ዘመን 14ኛ ሽንፈታቸው ነው።
እስከ አስር ካሉት ቡድኖች ይህ ትልቅ ቁጥር ነው።
በሚቀጥለው የውድድር ዘመንም ከአውሮፓ ውድድር ውጭ እንዳይሆኑ ያሰጋቸዋል።
በዚህ የውድድር ዘመን በኦልድትራፎርድ በዘጠኝ ጨዋታዎች ሽንፈትን አስተናግደዋል።
ይህም በአንድ ውድድር ዘመን በሜዳቸው ብዙ ከተሸነፉበት ቁጥር ጋር እኩል ነው። ከ1970-71 የውድድር ዓመት በኋላ በሁሉም ውድድሮች 82 ጎሎችን አስተናግደዋል።
“ማንችስተር ዩናይትድ አሁን በየጨዋታው የሚሸነፍበት መንገድ ከአሰልጣኙ ላይ ጥያቄዎች ያስነሳል” ሲል የክለቡ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ዋይኒ ሩኒ ለስካይ ስፖርት ተናግሯል።
“ተጫዋቾቹ ግን ራሳቸውን መመልከት አለባቸው ብዬ አስባለሁ። ለአንዳንድ ተጫዋቾች የውድድር ዘመኑ መጨረሻ አልደርስ ያላቸው ይመስላሉ።”
"ለኤሪክ ቴን ሃግ የሚጫወቱ ከሆነ በደንብ እያሳዩት አይመስለኝም።"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
'እጅን በጀርባ አድርጎ እንደመዋኘት ነው'
የቴን ሃግ የኦልድ ትራፎርድ የወደፊት እጣ ፈንታ በእርግጠኝነት አይታወቅም።
ውላቸው ሊጠናቀቅ አንድ ዓመት ቀርቶታል። የክለቡን ድርሻ በቅርቡ የገዙት ሰር ጂም ራትክሊፍ የእሑዱን ጨዋታ በስታዲየም ተገኝተው ተከታትለዋል።
ቢሊየነሩ አሰልጣኝ ለመቀየር ይፈልጋሉ የሚል ግምት እየጨመረ መጥቷል።
የቀድሞው የአያክስ አለቃ ቡድናቸው በዚህ የውድድር ዘመን የገጠመውን የጉዳት መጠን እንደጎዳቸው መረዳት ይቻላል።
ከእሁዱ ጨዋታ በኋላ "እያንዳንዱ አሰልጣኝ ሁሌም የተሻለ ነገር መስራት ይችላል።
እዚህ ከመጣሁ ሁለት ዓመት ቢሆነኝም አንድ ጊዜ ብቻ ነው ሙሉውን የቡድኑን የተጫዋቾች ለመምረጥ የቻልኩት” ብለዋል።
"እጅ በጀርባ ላይ አድርጎ፣ ጭንቅላትዎን ከውሃው ከፍ ማድረግ እንደመዋኘት ነው።"
ምንም እንኳን ዩናይትድ በዚህ የውድድር ዘመን በርካታ ችግሮች ቢኖሩትም በጉጉት የሚጠበቀው የኤፍኤ ካፕ የፍጻሜ ጨዋታ ከፊቱ አለ።
ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ደግሞ ማንቸስተር ሲቲ ነው።
ቡድናቸው ተስፋ አስቆራጩን የውድድር ዘመንን በጥሩ መንፈስ ለመጨረስ ከፈለገ የበለጠ መፋለም እንዳለበት ቴን ሃግ ያውቃሉ።












