ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የብራዚል የቀድሞ ፕሬዚዳንት የቀረበባቸውን የመፈንቅለ መንግሥት የሙከራ ክስ አስተባበሉ
የብራዚል የቀድሞ ፕሬዚዳንት ጄይር ቦልሶናሮ ስልጣናቸውን ከለቀቁበት አንድ ዓመት ጀምሮ በርካታ ፖለቲካዊ ጥቃቶችን እያስተናገዱ እንደሆነ ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ በሳኦ ፖሎ በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው እንደተናገሩት በእሳቸው ላይ እየቀረበባቸው ያለው የመፈንቅለ ክስ “ሐሰት” ነው ሲሉም ተናግረዋል።
በተጨማሪም በህዝብ ህንጻዎች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል ተብለው ለተከሰሱ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ምህረት እንዲደረግላቸውም ጠይቀዋል።
በአውሮፓውያኑ 2022 በተደረገው የብራዚል ምርጫ ከተሸነፉ በኋላ ቦልሶናሮ የከሸፈ የመንፈንቅለ መንግሥት አነሳስተዋል በሚል ፖሊስ ምርመራ እያደረገ ይገኛል።
የ68 ዓመቱ የቀድሞ ፕሬዚዳት በብራዚል ትልቋ ከተማ በነበረው የእሁድ የድጋፍ ሰልፍ ላይም በእርሳቸው ላይ የቀረበውን ክስ ፖለቲካዊ ዓላማ ያዘለ ነው ሲሉ አጣጥለውታል።
ብራዚል ያለፈውን ረስታ ለወደፊቱ እንድትራመድ እና እንድትቀጥል የማድረግ ጊዜው አሁን ነው ሲሉም ተደምጠዋል።
ቦልሶናሮ በዚሁ ንግግራቸውም ወቅት በቀጣዩ፣ በአውሮፓውያኑ 2026 አገሪቱ ስለምታካሂደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም ጠቆም አድርገዋል።
በብራዚል ያለውን የምርጫ ስርዓት አደጋ ላይ በመጣል እንዲሁም ያለምንም ማስረጃ ያለፈውን ምርጫ ተጭበርብሯል በማለታቸው የቀድሞው ፕሬዚዳንት ለስምንት ዓመታት ያህል በምርጫ እንዳይሳተፉም እግድ ተጥሎባቸዋል።
በብራዚል ሰንደቅ ዓላማ ቢጫ እና አረንጓዴ የለበሱ በርካታ ሰዎችም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሲናገሩ ለማዳመጥ ተሰብስበው ነበር።
ግዙፍ በተባለው የድጋፍ ሰልፍ ላይ በርካቶቹ የተገኙት ለነጻነት እንዲሁም በተለይም የመናገር ነጻነት ላይ ያላቸውን ድጋፍ ለመስጠት ነው።
ቦልሶናሮ “ሃሳባቸውን በግልጽ በመናገራቸው” እስር ቤት ለማስገባት ያለመ የማስፈራሪያ ዕቅድምም ነው በሚል በርካቶች ተችተዋል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የነበሩ በርካታ ደጋፊዎቻቸውም ያለፈው ምርጫ የተጭበረበረ ነው በሚል ያልተረጋገጡ ውንጀላዎችን በተደጋጋሚም ሲገልጹ ተደምጠዋል።
ደጋፊዎቻቸውን ይህንን የሚሉ ወይም እንደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያሉ ተቋማትን የሚተቹ ፓስተሮች እንዳያመጡም ቦልሶናሮ ጠይቀዋቸው ነበር ተብሏል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ ተገኝተው የነበሩት የ53 ዓመቱ የንግድ ዳይሬክተር አሌክሳንደር ፍራንሳ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በርካቶች በዚህ ስብሰባ የተገኙበት ምክንያት “ለአገራችን የምንፈልገውን ለመግለጽ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
የቦልሶናሮ ንግግር አመጽን የሚቀሰቅስ ወይም የምርጫ ስርዓቱን ሊያናጋ ይችላል በሚልም የብራዚል ባለስልጣናት ጉዳዪን በቅርበት እየተከታተሉት ይገኛሉ።
በአውሮፓውያኑ ጥቅምት 2022 የነበረውን ምርጫ ውጤት ለመቀልበስ ሞክረዋል እንዲሁም ወታደራዊ ኃላፊዎች የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራቸውን እንዲቀላቀሉ ጫና አድርገዋል በሚል ተከሰው ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑን ተከትሎም በዚህ ወር ፓስፓርታቸውን ማስረከብ ነበረባቸው።
በምርጫው በግራ ዘመሙ ፖለቲከኛ ሉዊዝ ኢናሲዮ ሉዳ ሲልቫ መሸነፋቸውን ተከትሎም በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በዋና ከተማይቱ ብራዚሊያ የሚገኘውን የፕሬዚዳንቱን ቤተ መንግሥት፣ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እና ምክር ቤትን ጨምሮ በርካታ የመንግሥት ህንጻዎችን ጥሰው በመግባት ዝርፊያ ፈጽመዋል እንዲሁም አውድመዋል ተብለዋል።
የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቦልሶናሮ ሶስቱ አጋሮቻቸው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የፖለቲካ ፓርቲያቸው ሃላፊም ታስረዋል። ይህም ደግሞ መፈንቅለ መንግሥት ሊፈጠር የሚችልበትን መድረክም አመቻችተዋል ሲልም ፖሊስ እየወነጀላቸው ይገኛል።