አወዛጋቢው አንድሪው ቴትና ወንድሙ በእስር እንዲቆዩ ፍርድ ቤት ወሰነ

አንድሪው ቴት እና ወንድሙ ትሪስታን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

አወዛጋቢና ጾተኛ የሚባለው አንድሪው ቴት እና ወንድሙ ትሪስታን በሮማኒያ በእስር እንዲቆዩ ፍርድ ቤቴ ብይን ሰጥቷል።

ወንድማማቾቹ ለአራተኛ ወርም በእስር ይቆያሉ ተብሏል።

አንድሪውና ትሪስታን በመድፈር፣ በህገወጥ የሰዎች ዝውውር እና የተደራጀ የወንጀል ቡድን አቋቁመዋል በሚልም ክስ እየተመረመሩም ይገኛሉ። ሁለቱም ወንጀሎቹን አልፈጸምንም ሲሉ አስተባብለዋል።

የአንድሪው ቴት ጠበቆች ደንበኛቸው እስከ ሚያዝያ መጨረሻ ድረስ በእስር እንደሚቆይ ተናግረዋል።

ቃለ አቀባያቸው ማቲያ ፔትሬስኩ ውሳኔው ቃል እንዳሳጣቸው ነው የተናገሩት።

የወንድማማቾቹ ጠበቆች በቡካሬስት ረቡዕ ዕለት በነበረው ዝግ ችሎት ላይ አቃብያነ ህግ ምንም አዲስ ማስረጃ አለማቅረባቸውን ተናግረዋል።

የደንበኞቻቸው ታዋቂነት በእስር እንዲቆዩ ለመወሰን የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ማቲያ ፔትሬስኩ እንዳሉት ዳኛው ለመጀመሪያ ጊዜ ከአገር ሊወጡ ይችሉ ይሆን ወይም ለህዝብ ስርዓት አደጋ ደቅነዋል ለሚለው ክርክር በቀጥታ ምላሽ እንዲሰጡም ነው የተጠየቁት።

ሆኖም ዳኛው በመጨረሻ ሁለቱም ወንድማማቾች እስከ ሚያዝያ ድረስ ለተጨማሪ 30 ቀናት በእስር እንዲቆዩ ወስኗል።

የቀጠለው እስር በወንድማማቾቹ ላይ ከፍተኛ ጥላሽት እንደቀባቸውና ስማቸውን ለማደስ ዓመታት እንደሚወስድም ተናግረዋል።

በአሜሪካ የአንድሪው ቴት ጠበቃ በቅርቡ ደፍሮኛል ያለችውን ተጎጂ ከነቤተሰቧ የምታቀርበውን ክስ ካልተወችው በ300 ሚሊዮን ዶላር በስም ማጥፋት ክስ እንደሚመሰረትባት አስፈራርተዋታል ተብሏል።

አንድሪው ቴት በቀደመ የስፖርት ሕይወቱ ከአንዴም አራት ግዜ የኪክቦክስ ውድድር የዓለም ሻምፒዮና ሆኗል።

አሁን ላይ ታዋቂ ያደረገው ግን በስፖርት ሕይወቱ ያገኘው ስኬት ሳይሆን ሴቶችን በተመለከተ የሚሰጣቸው “አጸያፊ ፣ ጾተኛ እና አስነዋሪ” የተባሉት አስተያየቶቹ ናቸው።

አንድሪው ቴት ሴቶችን በተመለከተ በሚሰጣቸው አስተያየት ከፌስቡክ፣ ከኢንስታግራም እና ከዩቲዩብ ታግዷል። ከትዊተርም እንዲሁ ታግዶ የነበረ ቢሆንም፣ ማኅበራዊ ሚዲያ በኤሎን መስክ ስር መግባቱን ተከትሎ ዳግም ወደ ማኅበራዊ ትስስር መድረኩ ተመልሷል።