የአሜሪካ ባንኮች ፈተና ውስጥ ቢሆኑም ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔን ጨመረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ማዕከላዊ ባንክ በድጋሚ የወለድ ምጣኔን ጨምሯል።
ባንኮች ወድቀት እየገጠማቸው ባለበት ጊዜ ይህንን እርምጃ መውሰድ የፋይናንስ አለመረጋጋትን ይፈጥራል ከሚለው ስጋት በተቃራኒ ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሷል።
ማዕከላዊ ባንኩ የባንክ ስርዓቱ ጠንካራና ችግርን መቋቋም የሚችል ነው የሚል ምክንያት በማስቀመጥ የወለድ ምጣኔውን በ0.25 በመቶ ከፍ አድርጓል።
ባንኮች እያጋጠማቸው ባለው ኪሳራ ምክንያት በመጪዎቹ ወራት የኢኮኖሚ ዕድገቱን ሊጎዳው እንደሚችልም አስቀምጧል።
ማዕከላዊ ባንኩ ዋጋን ለማረጋጋት የብድር ክፍያን እያሳደገ ነው።
ሆኖም ካባለፈው ዓመት ወዲህ እየተደረገ ያለው ቀጥተኛ የወለድ ምጣኔ ጭማሪ የባንክ ስርዓቱ ላይ ጫና አሳድሯል።
በዚህም ሳቢያ ሲልከን ቫሊ እና ሲግኒቸር የተባሉ የአሜሪካ ባንኮች ከፍተኛ የወለድ ምጣኔ ባስከተለው ችግር ምክንያት በዚህ ወር ኪሳራ አጋጥሟቸዋል።
የወለድ ምጣኔ መጨመሩ በባንኮች ያሏቸው ቦንዶች ዋጋ እንዲወርድ ሊያደረግ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
ባንኮች ከፍተኛ መጠን ያለው ቦንድ ስለሚይዙ ከፍ ያለ ኪሰራ ላይ የመውደቅ እድል አላቸው።
ባንኮች የያያዟቸውን ቦንዶች ለመሸጥ እስካልተገደዱ ድረስ የቦንድ ዋጋ መውረድ በራሱ ችግር አይደለም።
የወለድ ምጣኔ መጨመሩ በሰፊው የፋይናንስ እንቅስቃሴ ላይ አለመረጋጋትን አያመጣም ብለው የሚያስቡ የበርካታ ሀገራት መሪዎች አሉ። እንደነሱ እምነት ጭማሬው የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር የሚደረገው ጥረት ላይም ተጽዕኖ የለውም።
ባለፈው ሳምንት የአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ የወለድ ምጣኔውን በ0.5 በመቶ ጨምሯል።
የአንግሊዝ ባንክም የዋጋ ግሽበቱ ከባለፈው ወር በ10.4 በመቶ ባልተጠበቀ ሀኔታ መጨመሩ በተሰማ ማግስት ዛሬ የወለድ ምጣኔ ላይ የሚደረግ ጭማሬን ይፋ ያደርጋል።
የአሜሪካ መጠባበቂያ ጽህፈት ቤት ሊቀ መንበር ጄሮሜ ፖል መስሪያ ቤታቸው የዋጋ ንረትን መዋጋት ላይ እንደሚያተኩር ገልጸዋል። ሲልከን ቫሊ ያጋጠመወን ችግር ጠንካራ በሆነ የባንክ ስርዓት ውስጥ የተከሰተ ልዩ ሁኔታ ሲሉ ገልጸውታል።
ሆኖም አሁን ባንኮች ላይ ያጋጠመው ችግር ግን የኢኮኖሚውን እድገት እንደሚጎትት ገልጸዋል። ችግሩ የሚያስከትለው ተጽዕኖ ሙሉ መልክ ግን እስካሁን ግልጽ አይደለም።












