በኢትዮጵያ በኮሌራ በሽታ 23 ሰዎች መሞታቸው ተገለጸ

የታመመች ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

በኢትዮጵያ በቅርቡ በተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ምክንያት ከቀያቸው ከተፈናቀሉ የማኅበረሰብ አባላት መካከል 23 ሰዎች በኮሌራ በሽታ መሞታቸውን ሴቭ ዘ ቺልድረን የተባለው ድርጅት አስታወቀ።

መቀመጫውን በዩናይትድ ኪንግደም ያደረገው የሕጻናት አድን ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው የጎርፍ አደጋ እና ከፍተኛ ዝናብ በጣለበት በሶማሌ ክልል ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በበሽታው የተያዙ ከ770 በላይ ሰዎች መመዝገባቸውን አስታውቋል።

በበሽታው ምክንያት በሶማሌ ክልል ሞቶቹ የተመዘገቡት የጎርፍ አደጋ የውሃ እና የንጽህና መገልገያዎችን ካወደመ በኋላ ነው።

በቅርቡ በአገሪቱ የጣለው ከፍተኛ ዝናብ 1.5 ሚሊዮን ሰዎችን ለጉዳት የዳረገ ሲሆን ከ600 ሺህ ያላነሱትን ደግሞ ከመኖሪያቸው ማፈናቀሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታውቋል።

ምንም እንኳ ጎርፍ እና ከባድ ዝናብ ከአንድ ሚሊዮን በሚሆኑ ዜጎች ላይ ጉዳት ቢያስከትልም እስካሁን ድረስ የሰብዓዊ እርዳታ ድጋፍ ያገኙት ከ10 በመቶ እንደማይበልጡ ተመድ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ከ90 በላይ ወረዳዎች የኮሌራ በሽታ መቀስቀሱን ሪፖርት እንዳደረጉ የገለጸው የሕጻናት አድን ድርጅቱ፤ ከባድ ዝናብ ቢያንስ በሦስት ክልሎች መጣሉ ስለሚቀጥል ሁኔታዎች ከዚህም በላይ የከፉ ሊሆኑ ይችላሉ ሲል አስጠንቅቋል።

በቅርቡ ኤል ኒኖ እንዲሁም በሕንድ ውቅያኖስ በተከሰተው ዲፖል ተፈጥሯዊ ሁኔታ ምክንያቶች በኢትዮጵያ፣ በኬንያ እና በሶማሊያ ከባድ ዝናብ ጥሎ ከፍተኛ የጎርፍ መጥለቅለቅ ማስከተሉ ይታወቃል።

ባለፉት ሳምንታት በምሥራቃዊው ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ውስጥ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ ሳቢያ ከ30 በላይ ሰዎች ሲሞቱ፣ ከ20 ሺህ በላይ አባወራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የክልሉ ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተ ጎርፍ በሰው፣ በእንሰሳት እና በንብረት ላይ ከባድ ጉዳት ደርሷል።

በሶማሌ ክልል የአደጋ መከላከል ቢሮ የቅድመ ማስጠንቀቂያ አስተባባሪ የሆኑት አቶ በሽር አረብ ከሁለት ሳምንት በፊት ለቢቢሲ እንደገለጹት፣ የጎርፍ አደጋው በአጠቃላይ 10 ሺህ ሄክታር የሰብል መሬት ያወደመ ሲሆን፣ 3600 የቁም እንስሳትን ገድሏል።

በክልሉ የተከሰተው ጎርፍ ጉዳት ያስከተለው በአብዛኛው በወንዝ ዳርቻ አካባቢ ባሉ ወረዳዎች እንደሆነም ባለሥልጣኑ ተናግረዋል። ከባድ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋው ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ክስተት ያጋጣመው በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአጎራባቾች ሶማሊያ እና ኬንያ ጭምር ነው።

በዚህም ሳቢያ በአገራቱ ውስጥ የጎርፍ መጥለቅለቅ በሰዎች እና በንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ሰሞኑን የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ።