የቀድሞ ሚስቱን በቀጥታ ስርጭት ወቅት በእሳት አቃጥሎ የገደለ ቻይናዊ በሞት ተቀጣ

የፎቶው ባለመብት, DOUYIN
የቀድሞ ሚስቱን በቀጥታ ስርጭት ወቅት በእሳት አቃጥሎ የገደለ አንድ ቻይናዊ በሞት ተቀጣ።
ላሙ በመባል የምትታወቀው ግለሰብ ዱዪን በተባለው የቻይናዊያን የቲክቶክ አይነት ማህበራዊ ድር አምባ ታዋቂ ነበረች።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮቿ በሲቹዋን ግዛት ተራሮች ስለነበረው ህይወቷ ቪዲዮዎቿን ተከታትለዋል።
ክስተቱ በቻይና በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል።
አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ከቻይናውያን ሴቶች መካከል አንድ አራተኛ የሚሆኑት በቤት ውስጥ በደል ይደርስባቸዋል።
የሁለት ልጆች እናት የነበረችው ላሙ በትዳር ውስጥ በነበረችበት ወቅት ባሏ ያደረሰባተትን ጥቃት ለፖሊስ ቀርባ አቤት ብትልም የቤተሰብ ጉዳይ እንደሆነ ተነግሯታል።
ባለቤቷ ታንግ ሉ የሞት ፍርድ በተፈረደበት ወቅት ወንጀሉ “እጅግ ጭካኔ የተሞላበት” እና "በጣም መጥፎ" ማህበራዊ ተጽዕኖ ያለው ነው ሲል ፍርድ ቤቱ ገልጿል።
በአውሮፓውያኑ ሰኔ 2020 ላሙ ታንግን ሰማንያዋን ቀደደች። ፍርድ ቤቱ በእሷ ላይ በተደጋጋሚ ጥቃት መድረሱን ተናግሯል።
ከሦስት ወራት በኋላ በአባቷ ቤት ቤንዚን አርከፍክፎ አቃጥሏታል። 90 በመቶ ሰውነቷ ተቃጥሎ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ህይወቷ አልፏል።
ጉዳዩ በመላ ሃገሪቱ ቁጣን የቀሰቀሰ ሲሆን በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት በድጋሚ ወደ መድረክ እንዲበቃ ምክንያት ሆኗል።
በሺዎች የሚቆጠሩ የላሙ ተከታዮች በዱዪን ገጻቸው ላይ የሐዘን መልዕክቶችን አስተላልፈዋል። በኋላ ላይ ሳንሱር ተደረገ እንጂ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የዌይቦ ተከታዮችም ጉዳዩን ተቀባብለውታል።
ቻይና በአውሮፓውያኑ 2016 የቤት ውስጥ ጥቃትን ወንጀል ነው ብትልም በተለይም በገጠር አካባቢዎች አሁንም ሰፋት መኖሩ ይገለጻል።
አንዳንድ የመብት ተሟጋቾች በቅርቡ የተዋወቀውና ጥንዶች ከመፋታታቸው በፊት በግዴታ ለ30 ቀን አብረው መቆየት አለባቸው የሚለው “የማቀዝቀዣ” ጊዜ ሴቶች ከከፋ ትዳር ለቀው እንዳይወጡ ያደርጋቸዋል ሲሉ ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።












