የናይጄሪያ አየር ኃይል በስህተት ንጹሃን ላይ ሚሳኤል መተኮሱ ተገለጸ

ተዋጊ ጄት

የፎቶው ባለመብት, Nigerian Airforce

ታትሟል

የናይጄሪያ አየር ኃይል ንጹሃን ዜጎች ላይ ሚሳኤል በማስወንጨፍ ጉዳት ማድረሱ ተነገረ።

በአገሪቱ ሰሜን ምዕራብ በምትገኘው ካሲና ግዛት ነው ይህ ጥቃት የተፈጸመው።

አየር ኃይሉ ዒላማ ማድረግ የነበረበት የታጠቁ ኃይሎች ላይ ቢሆንም፤ ጥቃቱ ያረፈው ግን ንጹሃን ዜጎች ላይ መሆኑን ድርጊቱን የተመለከቱ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የአካባቢው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል አብዱልጃላል ሃሩን በጥቃቱ ቢያንስ አንድ ሰው ሲሞት በርካቶች ደግሞ ተጎድተው ሆስፒታል መግባታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ይህ ክስተት የተፈጸመው ታጣቂ ኃይሎቹ በጉዞ ላይ በነበረው የናይጄሪያ ወታደር ላይ ጥቃት ከፈጸሙ በኋላ ነው።

ይሁንና የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ እስካሁን የናይጄሪያ ጦር ያለው ነገር የለም።

ነገር ግን ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ በተመሳሳይ አካባቢ ሁለት “አሸባሪዎች" ተደብቀው በነበሩባቸው ካምፖች ላይ ድብደባ መፈጸሙን ገልጾ ነበር።

የታጠቁ ኃይሎችን ለመደብደብ በሚደረግ የአየር ጥቃት፣ በናይጄሪያ በስህተት ንጹሃንን መምታት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተደጋገመ የመጣ ክስተት ሆኗል።

ከእነዚህ መካከል ጎልቶ የሚታወሰው እአአ 2017 ላይ ከካሜሮን ድንበር አቅራቢያ በተፈናቃዮች እና በእርዳታ ሰራተኞች ላይ የደረሰው ጥቃት እና 100 አካባቢ ሰዎች የተገደሉበት ጥቃት ነው።