ጀርመንን ለአስርት ዓመታት አሸብሯል የተባለው የ’ሬድ አርሚ’ አባል ከ30 ዓመታት ፍለጋ በኋላ ተያዘች

ግለሰቧ ከ30 ዓመታት በፊት

የፎቶው ባለመብት, Interpol

የምስሉ መግለጫ, ግለሰቧ ከ30 ዓመታት በፊት
ታትሟል

ጀርመንን ለአስርት ዓመታት አሸብሯል የተባለው ‘ሬድ አርሚ ፋክሽን’ አባል የሆነች ግለሰብ ከ30 ዓመታት ፍለጋ በኋላ በቁጥጥር ስር ዋለች።

ፖሊስ ባደረገው ክትትል የ65 ዓመቷ ዳኒየላ ክሌቴ ሰኞ አመሻሽ ላይ በበርሊን በምትገኘው ክሩዝበርግ ግዛት ውስጥ ተይዛለች ተብሏል።

ከግለሰቧም በተጨማሪ ማንነቱ እስካሁን ያልተረጋገጠ ሌላ ግለሰብም በቁጥጥር ስር መዋሉ ተነግሯል።

ዳኒየላ ክሌቴ ጀርመንንን ለአስርት ዓመታት አሸብሯል የተባለው የግራ ዘመሙ ታጣቂ ቡድን አባልም ናት ተብሏል።

ግለሰቧ በግድያ ሙከራ እና በከባድ ዘረፋዎች ክስ ቀርቦባታል።

ከዳኒየላ ጋር በቁጥጥር ስር የዋለው ግለሰብ ከሷ ጋር በተመሳሳይ የዕድሜ ክልል ውስጥ ያለ የሚመስል ሲሆን ሃሰተኛ መታወቂያ ይዞ ነበር ተብሏል። ፖሊስ የግለሰቡን ማንነት እስካሁን ይፋ አላደረገም።

ግለሰቧ የተጠረጠረውን ዘረፋ ፈጽማበታለች ወደተባለው ብሬመን ግዛት በሄሊኮፕተር የተወሰደች ሲሆን ወደ ችሎት እስክትቀርብም ድረስ በእስር ትገኛለች።

ፖሊስ የጣት አሻራዎቿን በመጠቀም ማንነቷን ያረጋገጠ ሲሆን በቁጥጥር ስር ስትውልም ምንም ዓይነት ተቃውሞ አላሳየችም ተብሏል።

ከነዚህ ዓመታትም በኋላ ፖሊስ በቁጥር ስር ሊያውላት የቻለው ከጥቂት ወራት በፊት ከማህበረሰቡ በደረሰው ጥቆማ ነው።

ባለስልጣናቱ ግለሰቧ ለ30 ዓመታት ያህል እንዴት እንደተደበቀች፣ እንዲሁም ጀርመን ውስጥ ትኑር አትኑር፣ እንዲሁም የረዳት አካል ስለመኖሩም እንደማያውቁ ተናግረዋል።

ስትኖርበት የነበረው አፓርታማ የተፈተሸ ሲሆን ፖሊስ በዚህም ፍተሻ ጥይቶችን፣ ቀለሃዎችን እንዲሁም የእጅ ሽጉጥ ቢያገኝም ጠመንጃ አለማግኘቱን አስታውቋል።

ባለስልጣናቱ የግለሰቧ በቁጥጥር ስር መዋል “ሽብርተኝነትን” በማዋጋት ረገድ ትልቅ ምዕራፍ እንደሆነ ገልጸው “አሸባሪዎች” የቱንም ያህል ቢደበቁ ከመያዝ አያመልጡም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የተበታተነው ሬድ አርሚ የታጠቀ ቡድን ከአውሮፓውያኑ 1971 እስከ 1993 ባለው ጊዜ 34 ሰዎችን ገድሏል ተብሏል።

ቡድኑ የፖለቲካ አመራሮችን፣ የንግድ ኃላፊዎችን ዒላማ አድርጎ የነበረ ሲሆን ከሰለባዎቹም መካከል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የዶይቸ ባንክ ሊቀ መንበር ይገኙበታል። ። የዶይቸ ባንክ ኃላፊን በቦምብ ሲገድል፣ በቀድሞዋ ኮሚኒስት ምስራቅ ጀርመን የንግድ ስራን ወደ ግል የማዞር ኃላፊነት የተጣለባቸውን የመሃል ግራ ዘመም ፖለቲከኛ በመኖሪያ ቤታቸው ተኩሶ መግደሉም ተገልጿል።

በዚህም ወቅት ከ200 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውም ተነግሯል።

ባለስልጣናቱ ዳኒየላ በ1980ዎቹ እና 1990ዎቺ ውስጥ ንቁ ተሳትፎ የነበረው የሬድ አርሚ ሶስተኛ ትውልድ ተብሎ የሚጠራው እንቅስቃሴ አካል ነበረች ሲሉም ክስ አቅርበዋል።