ትራምፕ ሊያግዱት የነበረውን ቲክቶክን በመጠቀም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን አገኙ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዶናልድ ትራምፕ
ታትሟል

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሳሉ ቲክቶክን ለማገድ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ የነበሩት ዶናልድ ትራምፕ ማኅበራዊ ሚዲያውን ተቀላቅለው በአጭር ጊዜ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን ማፍራት ቻሉ።

ትራምፕ ቲክቶክን በተቀላቀሉ በ48 ሰዓታት ውስጥ ከአራት ሚሊዮን በላይ ተከታዮችን ማፍራት ችለዋል።

ትራምፕ እአአ 2020 ላይ ዋይት ሐውስ ሳሉ መተግበሪያው ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ጋር ግንኙነት አለው በሚል ምክንያት በፕሬዝዳንታዊ ትዕዛዝ በአሜሪካ እንዲታገድ አዘው ነበር።

ይሁን እንጂ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ጥረት በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች ውድቅ ተደርጓል።

በትራምፕ የተተኩት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም እንዲሁ ቲክቶክ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና አሰልፎ ይሰጣል በሚል በአሜሪካ እንዲታገድ ጥረት እያደረጉ ነው።

በቅርቡ የጆ ባይደን አስተዳደር ቲክቶክ እንዲሸጥ ካልሆነ ግን በአሜሪካ እንደሚታገድ ለማኅበራዊ ሚዲያው ባለቤቶች አማራጭ ሰጥቷል።

ዶናልድ ትራምፕ ከሥልጣን ከወረዱ በኋላ ቲክቶክ ላይ የሚደረገውን ጫና ሲቃወሙ ይስተዋላሉ። ፕሬዝዳንቱ ቲክቶክን ማገደ ትርፉ የፌስቡክ ባለቤት የሆነውን ሜታን ማጠንከር ብቻ ነው ይላሉ።

ትራምፕ የቲክቶክ አካውንት ከከፈቱ በኋላ “አሜሪካውያንን ለመድረስ የትኛውንም አማራጭ እጠቀማለሁ” ብለዋል።

ትራምፕ በሚቀጥለው ዓመት 2017 ዓ.ም. ኅዳር ወር ላይ በሚካሄደው የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ለሁለተኛ ዙር ሥልጣን ለመወዳደር በዝግጅት ላይ ይገኛሉ።

ከትራምፕ በተጨማሪ ጆ ባይደንም ለምርጫ ቅስቀሳ ቲክቶክን እየተጠቀሙ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የተከታዮቻቸው ብዛት ከትራምፕ ጋር ሲነጻጸር በ10 እጥፍ ያንሳል።

ቲክቶክ በአሜሪካ 170 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይገመታል። የማኅበራዊ ሚዲያው ባለቤት ባይትዳንስ የተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና አሳልፎ ይሰጣል በሚል በምዕራባውያን መንግሥታት የሚቀርብበትን ክስ አይቀበለም።

የትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ቡድን ቃል አቀባይ ካሮላይን ሌቪት የቀድሞ ፕሬዝዳንት የበርካታ ወጣቶችን ትኩረት ማግኘት መቻላቸውን እና ቲክቶክ ተጨማሪ ወጣቶችን ለመድረስ ጥሩ አማራጭ እንደሆነ ተናግረዋል።

ትራምፕ በአሁኑ ወቅት 4.8 ሚሊዮን ተከታዮች ያላቸው ሲሆን፣ በቲክቶክ ገጻቸው ላይ የለጠፉት የመጀመሪያ ቪዲዮ ከ77 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይቷል።

በሐምቡርግ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ተመራማሪ የሆኑት ማርከስ ቦሽ፤ ትራምፕ በሁለት ቀናት ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮችን ማፍራት የቻሉት ምናልባት የቲክቶክ ተጠቃሚዎች ማኅበራዊ ሚዲያው የመዘጋት ዕድሉን ትራምፕ ሊያስቀሩት ይችላሉ በሚል ሊሆን ይችላል ይላሉ።

ትራምፕ ከጥቂት ወራት በፊት ለሲኤንቢሲ ቴሌቪዥን ቲክቶክ ለብሔራዊ ደኅንነት ስጋት እንደሆነ እንደሚያምኑ የተናገሩ ሲሆን፣ መተግበሪያውን ማገዱ ግን “የሕዝብ ጠላት የሆነውን” ፌስቡክን የበለጠ ማጠናከር ነው ብለዋል።

ትራምፕ ከሜታ ጋር ጥሩ ወዳጅነት የላቸውም።

እአአ 2021 መጀመሪያ ላይ የተከሰተውን የካፒቶል ሂል አመጽ ተከትሎ የትራምፕ የፌስቡክ እና የኢንስታግራም ገጻቸው ታግዶ እንደነበረ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ ትራምፕ ‘ትሩዝ ሶሻል’ የተባለ የራሳቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ አገልግሎት እአአ 2022 መክፈታቸው ይታወሳል።